ኀዳር ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀንን ምክንያት በማድረግ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ከቃል ያለፈ በተግባር የተደገፈ አሰራርን እንዲከተል አሳስቧል። ሰመጉ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ከተቀበለች ከ68 ዓመታት በላይ እንደሆናትና መብቱ በሕገ መንግስቱ ውስጥ ቢካተትም ዜጎች ግን የሕግ ከለላው ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም ብሎአል።
እስካሁን ድረስ በአገሪቱ በከፋ ሁኔታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑንና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ዜጎች ድብደባ፣አካል ማጉደል፣ሕገ ወጥ ግድያዎች፣ከመጠን ያለፉ የኃይል እርምጃዎች፣አስተዳደራዊ በደሎች፣ሕገወጥ እስራት፣በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ባሉ ታራሚዎች ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች፣ ብሔር ተኮር ማፈናቀል፣በከተሞችና በውጪ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት ስም ዜጎችን ከቀያቸው በማፈናቀል የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች በከፋ ሁኔታ በመላ አገሪቱ እየተሳፋፉ በመምጣታቸው ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ ሳይሆኑ በአፋጣኝ ከቃል በዘለለ ተግባራዊ እርምጃዎችን መንግስት እንዲወስድ ሰመጉ በአቋም መግለጫው ጠይቋል።