ኀዳር ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አወዛጋቢው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃወም ከአመት በፊት አደባባይ የወጡ የኦሮምያ ክልል ወጣቶችና ተማሪዎች ህይወታቸው በመንግስት ታጣቂዎች ከተቀጠፈ በሁዋላ፣ ኢህአዴግ እቅዱን በድጋሜ ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀሱን ተከትሎ በአምቦ፣ በማንዲና በዙሪያ ከተሞችና ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ተቃውሞአቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ለኢሳት ደረሱት መረጃዎች እንደማለከቱት አካባቢው ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሁሉ በፌደራልና በኦሮምያ ፖሊሶች የተወረ ሲሆን፣ ተቃውሞውን ተከትሎ በመንዲ እስካሁን በደረሰን መረጃ 2 ወጣቶች ተጎድተዋል።
ወጣቶች ተቃውሞአቸውን መፈክሮችን በማሰማት እየገለጹ ሲሆን፣ ተቃውሞው ቂልጡ ካራ ወደሚባል ከተማ ተስፋፍቷል።በአምቦ ከተማ ፖሊሶች ተቃውሞውን በጭስ ለመቆጣጠር የሞከሩ ሲሆን፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከግቢ እንዳይወጡ ታግተው ውለዋል። ትምህርት ቤቶች በሙሉ መዘጋታቸውም ታውቋል።
የአዲስ አበባ አዲሱ ማስተር ፕላን በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ ከተሞችንና ቀበሌዎችን ወደ አዲስ አበባ የሚያስገባ ነው። በፖሊሲው መሰረት በርካታ አርሶአደሮች ከመሬታቸው ይፈናቀላሉ በማለት ተቃውሞአቸውን የሚገልጹት ወጣቶች፣ መንግስት ፖሊሲውን እንዲሰርዝ ይጠይቃሉ። የህወሃቱ ነባር ታጋይ አባይ ጻሃዬ ፖሊሲውን በግድ እናስፈጽማለን ብለው መዛታቸው ይታወቃል።