ኀዳር ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት ሁለተኛውን የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ከህዝብ ጋር ለመወያየት የጠራው ስብሰባ ህዝቡ ብሶቱን አሰምቶ በተቃውሞና ባለመግባባት ተጠናቋል።
የካራ ቆሬ ነዋሪዎች በመጀመሪያ የተደረገላቸውን ጥሪ ባለመቀበል በስብሰባው ባለመገኘታቸው፣ በድጋሜ 50 ብር እንደሚሰጥ ከተገለጸ በሁዋላ በ አዳራሹ ተገኝተዋል። ይሁን እንጅ ውይይቱ በእቅዱ ላይ መሆኑ ቀርቶ ህዝቡ ብሶቱን ሲያሰማ ውሎአል።
አንድ እናት ” የሰቆቃ ኑሮ ነው የምንኖረው፣ በአገራችን ሰላም አጥተናል። ለአገራችን ብንዋጋም አገር አልባ ሆነናል፣ መብታችን ይከበርልን” ብለው የተናገሩ ሲሆን፣ በህዝቡ መካከል ለዘመናት የነበረው መተሳሰብ እየጠፋ ወደ አደገኛ ሁኔታ እያመራ ነው ብለዋል። በውጭ አገር የምናየው አደጋ በእኛም አገር እንዳይመጣ እየሰጋን ነው በማለት፣ መንግስት እንዲያስብበት ጠይቀዋል።
የጸጥታው ጉዳይ ስጋት ላይ እንደጣላቸው የተናገሩት ሌላ እናት ደግሞ፣ ልጃቸው ከትምህርት ቤት ውላ ለመግባት መቸገሯን በመናገር መንግስት የለም በሚባልባት ደረጃ ተደርሶአል ብለዋል
ሌላ ተናጋሪ ደግሞ መንግስት የመሬት ወረራ እያለ ነዋሪዎችን ማፈናቀሉን በመቃወም ንግግር አድርገዋል። የአገራችን መሬት በውጭ አገር ሳይወረር እዚሁ በሰፈርንበት አገር መሬት ወራሪ እንባላለን በማለት የመንግስት የመሬት ፖሊሲ ተችተዋል
ሌላ አስተያየት ሰጪ በአዲስ አበባ ውሃ መብራት በመጥፋቱ መንግስት የለም በሚባልበት ደረጃ ተደርሷል ብለዋል
በተለይ ቦታንና ካርታን በተመለከተ በህዝቡና በአወያይ ካድሬዎች መካከል የተነሳው ውዝግብ መፍትሄ ባለማግኘቱ ህዝቡ ስብሰባውን እየረገጠ ለመውጣት ተገዷል። ስብሰባውም በጭቅጭቅ ተዘግቷል።