መንግስት በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ እድገት ማምጣቱን ቢናገርም አገራዊ ግቡ ዝቅተኛ ነው ተባለ

ኀዳር ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመንግስት አጠቃላይ የትምህርት ተደራሽነት ክንውን 43 ነጥብ 2 ብቻ መሆኑንና አሃዙ ከክልል ክልል እንደሚለያይ በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀ አንድ ሰነድ አመልክቷል።
የትምህርት ተሳትፎው በአዲስአበባ 88 በመቶ፣በትግራይ 75 በመቶ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ 45 በመቶ ሲሆን ፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ 3ነጥብ 6፣ አፋር 4 ነጥብ 5 እንዲሁም በጋምቤላ 17 ነጥብ8 በመቶ ብቻ ነው።
በተለይ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በ2007ዓ.ም አንደኛ ክፍል በዕድሜያቸው የገቡ ሕጻናት 37 እና 20 በመቶ ብቻ ነው።
የሁለተኛ ደረጃ አንደኛ እርከን ማለትም ከ9ኛ እስከ10 ትምህርት ጥቅል ተሳትፎ ምጣኔን በ2002ዓ.ም ከነበረበት 39 ነጥብ 1 በመቶ በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደ 62 በመቶ ለማድረስ ቢታቀድም በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ማድረስ የተቻለው 40 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ ነው።
ከ11ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለው ጥቅል የተማሪዎች ተሳትፎም ከነበረበት ስድስት በመቶ ወደ 11 በመቶ ብቻ ነው ማደግ የቻለው፡፡ በእዚህ የመሰናዶ ትምህርት ቅበላ ከአምስት ዓመት በፊት የነበረውን 204 ሺ ዓመታዊ የተማሪዎች ቅበላ በ2007 ዓ.ም ወደ 360ሺ ለማሳደግ ታቅዶ ከ449 ሺ በላይ ተማሪዎችን ወደ መሰናዶ ማስገባት ተችሏል።ይህ ከዕቅዱ አንጻር ሲታይ 25 በመቶ አብላጫ ውጤት የተመዘገበበት ነው።
በአገሪቱ የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ተሳትፎ ምጣኔ ከሌሎች መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ምጣኔ አንጻር ሲታይ ብዙ የሚቀረው መሆኑን የትምህርት ባለሙያዎች ይናገራሉ። በሁለተኛ ደረጃ ያለው የትምህርት ሽፋን በተለይ በኦሮሚያ፣በኢትዮጵያ ሶማሌና አፋር ክልሎች አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነው። ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል በአገሪቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት ሥራው ከአንደኛ ደረጃ የሚመጣውን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ተማሪ ሊሸከም በሚችል መልኩ አለመሆኑ ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አቅዶ አለመገንባት እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውና የትምህርት ቤቶቹ ምቹ አለመሆን የሚሉት ይገኙበታል።
በተመሳሳይ ዜና መንግስት የትምህርት ሽፋንን ማሳደጉን እና በስራው ውጤታማ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢናገርም ዘጋቢያችን ወደ አማራ ክልል ዋግ ህምራ ብሄረሰብ አሰተዳደር ዞን የብአዴንን 35ኛ ዓመት ለማክበር የትግል ሜዳዎችን ባስጎበኝበት ምዕራፍ በመገኝት በዛፍ ስር የሚማሩ ተማሪዎችን ፎቶ አንስታ ልካለች።
የዓይን እማኞች በሰጧት ቃል በተመሳሳይ ሰሜን ወሎ ፤ ደቡብ ወሎ ፤ ዋግ ህምራ ፤ ደቡብ ጎንደር አካባቢዎች ያሉ ከዋና መንገድ ዳር በአስር ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኙ የገጠር ትምህርት ቤቶች በዛፍ ስር የሚካናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡