ጥቅምት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የገዢው መንግስት የውስጥ ችግሩን በሰለጠነ አካሄድ ከመፍታት ይልቅ በጦር ኃይሉ ቁጥርና የመሳሪያ ብዛት ለማስፈራራት የጀመረውን አካሄድ ከማጠናከር በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች እየሞከረ ያለው የሰራዊት ምልመላ እንዳልተሳካ የድርጅቱ የቀድሞ ታጋዮችና ተሰናባች የሰራዊቱ አባላት በተለይ ለኢሳት ተናገሩ፡፡
ከድርጅቱ ጋር በመወገን ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉት ተሰናባች የሰራዊቱ አባላት እንደተናገሩት ረዢምና መራራ ትግል በማድረግ ከሰራዊቱ ከተሰናበቱ በኋላ የክልሉ መንግስት የሰጣቸውን ድጎማ ተቀብለው ወደ መኖሪያ ቀያቸው ቢሔዱም በአካባቢው የሚሰራውን የመልካም አስተዳደር ችግር በመቃወም ባሳዩት አቋም በማነኛውም ስራ እንዳይወዳደሩ ማዕቀብ እንደጣለባቸው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በርካታ የተመላሽ ሰራዊት አባላት በስቃይ ላይ እንደሆኑ የሚናገሩት የቀድሞሰራዊት አባላት ከኮንትራት ስራ ጀምሮ የሰራዊቱን አባላት ከማሳተፍ ይልቅ ሃብትና ንብረት ያላቸውን የአመራር ቤተሰቦችን መቅጠርና በትርፍ ሰዓታቸው ማሰራት በወረዳ አካባቢ የሚገኙ የገዢው መንግስት መራሮች ሲሰሩት የሚታይ የዕለት ከዕለት አሰራር መሆኑ በተመላሽ ሰራዊቱ ላይ ሃዘንን የፈጠረባቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህንን በማይት በመንግስት ስራ ላይ የተሰማሩ የቀድሞ ተመላሽ አባለት ተቃውሞ ሲያቀርቡ ‹‹ እናንተ ለነሱ ጠበቃ ልትቆሙ ነወይ? ›› የሚል ዛቻ ከአመራሩ አካባቢ እያጋጠማቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
በገጠር አካባቢ ያለው ወጣትም ከትግል የተመለሱት ስራ አጥተው በየመንገዱ ሲቸገሩ እየተመለከተ ለመከላከያ ሰራዊትነት እጁን መስጠት ባለመፈለጉ ገዢው መንግስት ሰራዊት ለመመልመል በተደጋጋሚ የሚያደርገው ሙከራ እንደማይሰካለት አባላቱ ተናግረዋል፡፡
በአጎራባች ክልሎች ለተመላሽ ሰራዊቱ እየተደረገለት ያለውን እንክብካቤ ለማየት ዕድሉን ያገኙት የቀድሞ የሰራዊቱ አባላት በክልላቸው የዚህ አይነት እንክብካቤ ቀርቶ የእለት እንጀራ ለማግኘት የሚያስቻላቸው ድጋፍ እንዳላገኙ እየተመለከተ ወጣቱ ለምን ይመለመላል በማለት የሰራዊት ቅጥሩ በበርካታ አካባቢዎች እንዳልተሳካ ተናግረዋል፡፡ በዛላምበሳና ቡሬ ግንባር በመዋጋት በፈንጅ ተመተው በሰውነታቸው ውስጥ አራት ፍንጣሪ ተሸክመው እንደሚኖሩ የሚናገሩት ሌላው ተመላሽ ሰራዊት ያላቸውን ቅሬታ ሲያቀርቡ፣ ወደሃገራቸው ከገቡ በኋላ ለዕለት ጉርስ መጠቀሚያ የሚሆን አነስተኛ የአትክልት ቦታ ከተሰጣቸው በኋላ በግቢው ጎጆ ቀልሰው በመኖር ላይ እያሉ ሳይታሰብ ተነስ በመባላቸው ከአምስት ቤተሰባቸው ጋር መድረሻ ማጣታቸውን ይናገራሉ፡፡
ከነቤተሰቦቻቸው ጋር ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ የሚናገሩት ተመላሽ አባሉ ፣ በከተማ ዳርቻ ላይ እንዲገለገሉበት ከሰባት አመት በፊት ተሠጠው ያለሙትን ቦታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ለዕለት ሆዳቸው መሙያ አማራጭ ሳይሰጣቸው ልቀቅ በመባላቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ እየደረሰባቸው መሆኑን በምሬት ይናገራሉ፡፡
ዕድሜያቸው ለስራ ያልደረሱ አራት ልጆች አባት የሆኑት ተመላሽ ሰራዊት በተደረገባቸው ተጽዕኖ በመማረር ራሳቸውን ለማጥፋት እስከ መፈለግ ደረጃ የደረሱበት ሁኔታ እንደነበረ በሀዘን ይናገራሉ፡፡
ከሰራዊቱ በተመለሱ ጊዜ የእርሻ ቦታ ለገጠሩ ለከተማው ተመላሽ ድጋፍ ይደረጋል ቢሉም ከስድስት ሽህ ብር ውጭ ተጨማሪ ነገር ባለማግኘታቸው አብዛኛው ተመላሽ ሰራዊት ገንዘቡን ለዕለት ችግሩ በማዋል ባዶ እጃቸውን መቅረታቸውን ቅሬታ አቅራቢው ገልጸው፣ አሁን የመኖሪያና ስራ ቦታቸውን እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው በመሆኑ መጠጊያ በማጣት ከነልጆቻቸው ጎዳና ላይ ለመውጣት እንደተገደዱ ይናገራሉ፡፡
በፈንጅ ወረዳ እንደ ውሻ የፈንጅ ማምከኛ በመሆን፣በውሃ ጥምና ረሃብ የተንገላቱት ተመላሽ ሰራዊቶች ፣ ገዥውን መንግስት ለዚህ ካበቁ በኋላ ዛሬ ያ ሁሉ ተረስቶ ሰራዊቱ እየተንገላታ እየታየ ወጣቱ ለውትድርና ለመመልመል ምንም ፍላጎት እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ዛሬ ለሰራዊትነት እንዲመለመል የሚጠየቀው ወጣት እኛን በሚያይበት ጊዜ ‹‹ ደማቸውን አፍስሰው ለመጡት የቀድሞ ታጋዮች ምን ተደረገላቸው ? ›› የሚል ጥያቄ እያነሳ መሆኑን ተጎጅው ሰራዊት ተናግረዋል፡፡
ገዢው መንግስት ሰራዊት ለመመልመል በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው ማስታወቂያዎች እንዳልተሳካ ሲመለከት፣ ማስታወቂያዎችን በመቀያየር ለአየር ሃይል፣ለኤሌክትሮኒክስ ዋርፌርነት በማለት ወጣቱን ለማታለል የሚያደርገውን ሙከራ አጠናክሮ ቢቀጥልም በየአካባቢው ያለው ወጣት በእምቢተኝነቱ መቀጠሉን የክልሉ ነዋሪዎች ተናግረል፡፡