በኢትዮጵያ ድርቁ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ

ጥቅምት ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በፓስፊክ ውቅያኖስ መሞቅ ሳቢያ የሚከሰተው በኤሊኖ የአየር መዛባት ተከትሎ ከሰሃራ በታች ባሉት አገራት በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ከፍተኛ በሆነ የምግብ እጥረት ሰለባ እንደሆኑና የዕርዳታ ለጋሽ አገሮች እርዳታውን በአፋጣኝ ካልሰጡ አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችል ሰኞ እለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
በአስር ዓመት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አሰቃቂ ችጋር በኢትዮጵያ መከሰቱንና የበልግ እና የክረምቱ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡ ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ አፋጣኝ የሆነ ዕርዳታ ያስፈልገዋል።በምግብ ዕጥረቱ ሳቢያ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ሕፃናት እየሞቱ እንደሆኑና ወደ ሆስፒታል እየተወሰዱ መሆናቸውንና በመስከረም ወር ብቻ ከ35,000 ሽህ በላይ አዲስ ርሃብተኛ ሕፃናት በተጨማሪ መኖራቸውንና ከ250,000 ሽህ በላይ ሕጻናት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይህም በቀጠናው ክብረወሰን የሰበረ ረሃብ መከሰቱን ማሳያ እንደሆነ አስረድተዋል።
በምስራቅ አፍሪካ 22 ሚልዮን በላይ ሕዝብ በመጪው አዲስ ዓመት አፋጣኝ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገውና ከእዚህ ውስጥ 15 ሚሊዮን የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን የድርቁ ሰለባ መሆናቸውን ገልጾ ይህም በመቶኛ 15 % የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያዊያን የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን አሃዙ ያመላክታል ሲል ድርጅቱ የጉዳዩን አሳሳቢነት በጥናቱ መግለጹን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።