ኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር ሁከት ተቀስቅሶ ከአስር ሰዎች በላይ ተገደሉ

ጥቅምት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኬንያዋ የድንበር ከተማ ሜሩ ኢዞሎ አቅራቢያ በቦረና እና ሜሩ ጎሳዎች መሃከል በተቀሰቀሰ ግጭት አስር የአካባቢው ነዋሪዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ ከ2 ሺ በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
የከተማው አሽከርካሪዎች ግጭቱ እጅግ አስፈሪ እንደነበርና ሁኔታዎቹ አሳሳቢ መሆናቸውን ገልጸው የሜሩ ብሔር አባላት ወደ ከተማቸው የሸሹ ሲሆን የቦረና ጎሳ አባላትም ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ ታግደዋል።
በግጭቱ ምክንያት መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ በመሆናቸው የእለት ከእለት እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል።ሱቆች ተዘርፈዋል፣ትምህርት ቤቶችና ባንኮች ተዘግተዋል ።የሚሩ ብሔራዊ ፓርክም አገልግሎቱን አቋርጧል።ስራ አጥነትነት በፈጠረው ተስፋ መቁረጥ ከፍተኛ የሆነ ድህነት፣በሙስና ምክንያት የወደፊቱ የኬንያ መጻኢ እጣፋንታ አሳሳቢ መሆኑንና በምጣኔ ሃብት ገቢ አለመመጣጠን ሳቢያ ወደ ሕዝብ ለሕዝብ እልቂት አገሪቱ እንዳታመራ ያሳስባል ሲሉ የፍትሕ ቢሮ ኃላፊው ዶክተር ዊሊ ሙቱንጋ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው እንደ አውሮፓዊያን ዘመን አቆጣጠር የ2007 – 2008 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ 1,100 ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውና ከ600,ሺ በላይ የሚሆኑት ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል ሲል ስታንዳርድ ዲጅታል ኒውስ አክሎ ዘግቧል።