ከ30 አመታት ወዲህ አስከፊ ነው ለተባለው ድርቅ እርዳታ ቢቀርብም በቂ አይደለም ተባለ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ክፍል ባወጣው ዘገባ፣ አገሪቱ ለገጠማት አስከፊ ረሃብ አንዳንድ የምእራብ አገራት እርዳታ እያደረጉ ቢሆንም፣ እርዳታው አሁንም በቂ አይደለም ብሎአል።
አንዳንድ መንግስታት ለልማት በሚል ለመንግስት ሊሰጡት ያሰቡትን እርዳታ፣ለተጎጂዎች ለማዋል እያሰቡ መሆኑንም መጽሄቱ ገልጿል። በሶማሊ ክልል በኤሚ ወረዳ የሸበሌ ወንዝ በከፍተኛ ሁኔታ በመሙላቱ 700 የሚጠጉ ሰዎች በምስራቅ ኤሚ ወረዳ መጠለላቸውንና እርዳታ እየተጠባበቁ መሆኑን መጽሄቱ ዘግቧል።
በተመሳሳይ ዜናም በዘንድሮው ድርቅ ያጋጠመውን የእንስሳት ሞት አስቀድሞ የመቀነስ ስራ አለመከናወኑን የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው አምነዋል፡፡
ሚኒስትሩ ሰሞኑን ለንባብ ለበቃው መንግስታዊው ዘመን መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለልልስ በዘንድሮ ድርቅ በተለይ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የእንስሳት ሞት ማጋጠሙን በመጥቀስ የአደጋ መከላከልና ማስጠንቀቂያ ስርዓታችን በጣም ጠንካራና በአፍሪካ ምርጥ የሚባል ቢሆንም አርብቶአደሩ አካባቢ ያለው አኗኗር የተበታተነ ስለሆነ ከዚህ አንጻር አፈጻጸሙ ውስንነት ነበረው ብለዋል፡፡
ችግሩ ሲከሰትም በእንስሳት ላይ የደረሰውን ሞት የመቀነስ ስራ መስራት ይቻል እንደነበር በመጥቀስ በተዘዋዋሪ ችግሩን የመቀነስ ስራ በመንግስት በኩል አስቀድሞ አለመከናወነን አምነዋል፡፡
በእንስሳቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት ከመድረሱ በፊት እንስሳቱን ውሃና ግጦሽ ወደአለበት አካባቢ ማንቀሳቀስ ወይንም የመኖ አቅርቦቱን በማረጋገጥ የድርቅ ጊዜው እስኪያልፍ ድረስ ሰውነታቸው ተጠብቆ እንዲቆዩ ማድረግ ይቻል እንደነበር ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡በሌላም በኩል ሁሉንም እንስሳት እየቀለቡ ማቆየት ስለሚያስቸግር ገበያው የሚቀበለውን
ያህል በሽያጭ በማቅረብ መቀነስ ይቻል እንደነበር ተናግረው፣ በዚህ አካባቢ ለተፈጠረው ችግር መኖና ውሃ በማቅረብ ችግሩን መፍታት አይቻልም ያሉት ሚኒስትሩ በእኛ በኩል የተደረገው ግን ይህ ነው፣ በዚህ ምክንያት በርቀት ባሉ አርብቶአደሮች አካባቢዎች መድረስ ሳይቻል በመቅረቱ ያሉት እንስሳት ወደመፍትሄ ከመድረሳቸው በፊት ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲሉ የመንግስታቸውን ድክመት ተናግረዋል፡፡
ሰዎችን በተመለከተ ግን ረጂዎች ፈጥነው ምላሽ ባይሰጡም በሁሉም አካባቢዎች የምግብ አቅርቦቱ አለ ያሉት. ሚኒስትሩ በተለይ በአርብቶአደር አካባቢዎች እንስሳት ስለተጎዱ ከእንስሳት ተዋጽኦ የሚያስፈልጉ አቅርቦቶች(ወተትና ስጋ) በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው ሕጻናትና የሚያጠቡ እናቶች ተጎጂ ሆነዋል ብለዋል። ለእነዚህ ወገኖች አልሚ ምግቦች እየቀረቡ ነው ሲሉ አክለዋል።
በአሁኑ ወቅት በተከሰተው የድርቅ ችግር የተጎዱት በተደጋጋሚ ለእርጥበት እጥረት የሚጋለጡ አካባቢዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ፣ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲከሰት ቅድሚያ የሚጋለጠው ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ህዝብ ነው ይላሉ፡፡ ከድህነት በታች የሚኖረው ሕዝብ 20 ሚሊየን እንደሚደርስ የጠቆሙት አቶ ተፈራ፣ አብዛኛው ህዝብ የሚኖረውም በገጠር መሆኑን፣ ይህ የህብረሰተብ ክፍል እንደአልኒኖ ያለ ውጫዊ ተጽዕኖ ሲመጣበት ያለልክ ይጎዳል በማለት አስረድተዋል፡፡
ሆኖም ሚኒስትሩ ባለፉት 20 ዓመታት በሰልጣን ላይ የቆየው መንግስታቸው የድርቅን ችግርን ለመቋቋም የሚያስችል ስራ ለምን ማከናወን ሳይችል እንደቀረ ለመጽሄቱ ዘጋቢ ያሉት ነገር የለም፡፡