ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቅዳሜ ጥቅምት 13 2007 ዓም በተካሄደው በዚህ ዝግጅት ላይ ነዋሪነታቸው በኪዊንስላንድ ግዛት የሆኑ የሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የታደሙበት ሲሆን ለንደን ከሚገኘው የኢሳት ማሰራጫ ጣቢያ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ቀጸላ ተገኝታ ከነዋሪዎቹ ጋር ውይይት ተካሂዷል። ዝግጅቱን በቡራኬ የከፈቱት በብሪዝበን የደብረ ጸሃይ ቅዱስ ጊዎርጊስ ቤ/ክ አስተዳዳሪ ቀሲስ መንግስቱ ሃይሉ ሲሆን እሳቸውም ከቡራኬው አስከትለው ባደረጉት ንግግር ሃገራችንና ህዝቧ በአሁኑ ወቅት እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን አውስተው ለተገፉት ድምጽ በመሆን እውነትን እያወጣ ያለውን ኢሳትን ሁላችንም መደገፍ እንደሚገባን አሳስበው፤ እውነትን ከያዘ ጎን መቆም በራሱ ሃይማኖታዊ ስራና ግዴታም ጭምር መሆኑን አክለው ተናግረዋል።
በማስከተል ዝግጅቱን በማስመልከት ንግግር ያደረገችው የዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ተወካይ ወ/ሮ ሰብለ ወርቅ ታደሰ ስትሆን፤ በእለቱ የተገኙትን ታዳሚዎችን በማመስገን “ሁልግዜም ቢሆን ጥቂቶች ግን ደግሞ የቆረጡ እነሱ ታሪክ ሰሪዎች ናቸው” ካለች በኋላ ኢሳት ለዛሬዋ እለት እንዲደርስ በማስቻላችሁ ልትኮሩ ይገባል፡፡ ለቀጣይነቱም አስተዋጾዋችንን በተሻለ መልኩ ማድረግ እንደሚገባን ለተሰብሳቢው አሳስባለች። የኢሳት ባልደረቦች እየከፈሉት ያለውን በገንዘብ ሊተመን የማይችለውን አስተዋጾ በማውሳትም እንዲህ ሙሉ ጊዜአቸውንና አቅማቸውን እየሰጡ ያሉትን ባለሙያዎች አቅም በፈቀደው መርዳት ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን ወ/ሮ ሰብለወርቅ አክላ ተናግራለች። የተሻለ ቀን ለማየት የምንናፍቅ ወገኖች ሁሉ በጋራ መስራት ይገባናል ስትልም ጥሪዋን አቅርባለች።
በመቀጠል መድረኩን የተረከበችው በለንደን የኢሳት ባልደረባ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ቀጸላ ነበረች። መታሰቢያም የኢሳት አስፈላጊነት ላይ በማተኮር የተሰራ አጭር የዳሰሳ ጥናት ለተሰብሳቢው አቅርባለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመንተራስ ያደረገችውን የዳሰሳ ጥናት መሰረት በማድረግ እንደገነጸችው ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛና አማራጭ የሚሆን የመረጃ ምንጭ ባለመኖሩና እንዲኖርም ባለመፈቀዱ ህዝቡ በመረጃ እጦት ተቀፍድዶ ያለበት ወቅት ነው። በመሆኑም ኢሳትና ኢሳትን የመሳሰሉ አማራጭ የሚድያ ተቋማትን ማግኝት የግድ መሆኑን ገልጽለች። አስከትላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በታላቁ ወመዘክር ውስጥ የሚገኙ ታላላቅ የታሪክ መጻህፍትና መዛግብት እንዲወድም እየተደረገበት ባለበት፤ ትውልዱ ስለሃገሩ ታሪክ የሚያውቅበት መንገዶች ሁሉ እየተዘጉበት ባለበት በአሁኑ ወቅት ታሪካችንን ለማወቅና ለመጪው ትውልድ ታሪክን ለማስተላለፍ እንደ ኢሳት ያሉትን ሚዲያዎች ይኖሩን ዘንድ የግድ እንደሚል ተናግራ በተለይም ኢትዮጵያዊ ስነ ምግባርና ግብረ ገብነትን ከትውልድ ወደትውልድ እንዳይተላለፍ ለማጥፋትና ትውልዱን በማንነት ቅዥት ውስጥ እንዲባዝን ለማድረግ እየተደረገ ካለው እኩይ ስራ ለመታደግና ለማስተማር ኢሳት ተግቶ እየሰራ መሆኑን ዘርዝራ፤ ይህንን ሁሉ የታሪክና የትውልድ ሃላፊነት ለመወጣት ታድያ ኢትዮ ጵያን እንወዳለን የምንል ሁሉ ልንረባረብና የራሳችንን ድርሻ በሚያስፈልገው ሁሉ መወጣት እንደሚኖርብን አሳስባለች።
መታሰቢያ በማስከተል ስትናገር ኢሳት ባለው የሰው ሃይል እጥረትና ተያያዥ ችግሮች የተነሳ የሚፈለገውን ያህል ባያረካችሁም እያደረገ ያለው አስተዋጾና ለህዝብ ያለው ተደራሽነት ግን መገመት ከሚቻለው በላይ ስኬታማ እንደሆነ ገልጻ ይህም ስኬት የተገኘው ሃገር ቤትና በመላው አለም በሚገኙ ቆራጥ ኢትዮጵያውያን አማካኝነት መሆኑን ገልጻ ምስጋናዋን ያቀረበች ሲሆን ከኢሳት ማኔጅመንት ኮሚቴ የተላከውንም የምስጋና የምስክር ወረቀትም አስረክባለች።
በእለቱ ከተሰብሳቢዎች አንዳንድ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ተነስተው ተንሸራሽረዋል።
በመጨረሻም ለእለቱ በጨረታነት የቀረበው የታላቁ ሰማእት የአቡነ ጴጥሮችን ምስል የሚያሳይ የፎቶ ስራ ሲሆን ከታዳሚዎች ውስጥ በቅዱስ ጊዎርጊስ ስም የተጫረተ ግለሰብ በማሸነፉ የቅዱስ ጊዎርጊስ ቤ/ክ አገልጋይና የሰበካ ጉባኤው ተወካዮች ስእሉን ተረክበዋል።
በመቸረሻም እንደ አከፋፈቱ ሁሉ መዝጊያውም ቀሲስ መንግስቱ ሃይሉ ጸሎተ ቡራኬ በመሰጠትና የዝግጅቱ ታዳሚዎችንና አዘጋጆችን በማመስገን ተጠናቋል።