በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት እነ ዘመነ ምህረት ስርዓቱን በፍርድ ቤት አወገዙ

ጥቅምት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አቶ ጌትነት ደርሶ ” ‹‹ሽብር ተፈፅሞብኛል እንጅ አሸባሪ አይደለሁም››፣ ‹‹ፍትህ ቢኖር ኖሮ እኔ ሳልሆን ወያኔና ግብረ አበሮቹ ነበሩ እዚህ መቆም የነበረባቸው›› ሲል፣ አቶ ዘመነ ምህረት ደግሞ ” ‹‹የተከሰስኩት ድርቡሽ እንኳ ያልደፈረውን የጎንደር ጥምቀት ላይ ፈንጅ ልታፈነዳ ነበር ተብዬ ነው፡፡ ምርመራ ላይ ግን ለምን የመኢአድ አባል ሆንክ ይሉኛል›› ማለቱን ለኢሳት የደረሰው የፍርድ ቤት ውሎ የድምጽ ማስረጃ አመልክቷል።
ተከሳሾች ጥቅምት 12/2008 ዓ.ም የእምነት ክህደት ቃላቸውን በሰጡበት ወቀት ጠንካራ ገዢውን ፓርቲ የሚያወግዙ ጠንካራ ንግግሮችን አድርገዋል። አንደኛ ተከሳሽ አቶ ዘመነ ምህረት የጎንደር ጥምቅት ላይ ፈንጅ ሊያፈነዳ እንደነበር መከሰሱን ሲገልፅ ‹‹ሰው አይደለም እንሰሳት እንኳን የማይደፍሩትን፣ ድርቡሽ እንኳን ያልደፈረውን ጥምቀት እኔ በክርስትና ሀይማኖትና ባህል ተኮትኩቼ ያደኩትን ሰው ፈንጅ ልታፈነዳበት ነበር መባሌ ያሳዝናል›› ሲል ተናግሯል፡፡ በምርመራ ወቅት ‹‹ለምን የመኢአድ አባል ሆንክ? ለምን የኢህአዴግ አባል አልሆንክም?›› እንደተባለ የገለፀው አቶ ዘመነ ፣ ክሱ እሱን ለማሰር የተቀነባበረ ሴራ መሆኑን ገልፆል፡፡ አቶ ዘመነ ” የታሰረው ኤርትራ እንዳትገነጠል ሲታገሉ የኖሩትን፣ እንዲሁም የሰላማዊ ትግሉ ፈር ቀዳጅ የሆኑት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ያስጀመሩትን ትግልን የመኢአድ አመራር ሆኖ እያስቀጠለ በመሆኑ እንደሆነ” ተናግሯል፡፡ ወንጀሉን እንዳልፈፀመው የገለጸው አቶ ዘመነ ፣ ‹‹ከተጠቀሰው መካከል የማምነው አለኝ፣ ይህም ዛሬም ነገም ኢህአዴግን እንደምታገለው የሚለው ነው›› ብሏል፡፡
2ኛ ተከሳሽ የሆነው አቶ ጌትነት ደርሶ በበኩሉ ‹‹ሽብር ተፈፅሞብኛል እንጅ እኔ አሸባሪ አይደለሁም›› ያለ ሲሆን፣ ‹‹ፍትህ ቢኖር ኖሮ እዚህ መቆም የነበረኝ እኔ ሳልሆን ፣ መሳሪያን ተገን አድሮጎ ለ3 ወር ጨለማ ቤት ዘግቶ ጭካኔ የፈፀመብኝ ወያኔና ግብረ አበሮቹ ነበሩ ” ብሎአል። ተከሳሾች አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለፍርድ ቤት በጻፈው ደብዳቤ አቶ አንዳርጋቸው ቃሊቲ የሉም ብሎአል። ዳኛው ምን እናድርግ ጠቁሙን ያሉ ሲሆን፣ ተከሳሾች አቶ አንዳርጋጀው ባሉበት ቦታ ተፈልገው ይቀርቡልን ማለታቸውን ከድምጽ ማስረጃው ለመረዳት ይቻላል
ዛሬም በድጋሜ አቤቱታውን ያቀረበው አቶ ዘመነ ምህረት ‹‹እኛ እየራበን ነው፡፡ ምግቡን እንሰሳት እንኳን ሊበሉት አይችሉም፡፡ ቤተሰቦቼ እንዳይጠይቁኝ ተደርጓል፡፡›› በማለት ከተያዙበት ጥር 10/2007 ጀምሮ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
የዘር መድሎ እየደረሰባቸው እንደሆነ እና ሽንት ቤት ጥግ እንዲተኙ መደረጋቸውንም ለፍርድ ቤቱ ያመለከተው አቶ ዘመነ፣ ለፍርድ ቤቱ ቅሬታ በማቅረቡም ከማረሚያ ቤቱ ስቃይ ሊገጥመው እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።
በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የሰው ምስክር ለማቅረብም ለህዳር 3/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ስለድምጽ ጥራቱ ይቅርታ እንጠይቃለን። ድምጹን ቀርጸው ለላኩልን ከፍተኛ መስጋና እናቀርባለን
በሌላ ዜና ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ መራዓዊ ከተማ የቀበሌ 03 ዋና አስተዳዳሪ ፣ምክትል አስተዳዳሪና የሰው ሀብት አስተዳደር አቶ አባት አውለው፣ ምክትል አስተዳዳሪ መለሰ ሞላ እና የሰው ሀብት አስተዳደር ይግዛው ስንሸው የግንቦት7 አባላት ናቸው በሚል መታሰራቸውን ዘግይቶ የደረሰን ዜና አመልክቷል።