ሙስሊሙ ማህበረሰብ በመንግስት ላይ ቅሬታውን እየገለጸ ባለበት ወቅት መጅሊሱ የጸሎት ስነስርአት አደረገ

ጥቅምት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሳውድ አረቢያ በጸሎት ስነስርአት ላይ በነበሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን ከፍተኛ አደጋ ተከትሎ መንግስት የሃዘን መግለጫ ባለመውጣቱና ሰንደቅ አላማም ዝቅ ብሎ ባለመውለብለቡ የሃይማኖቱ አባቶች ቅሬታቸውን እየገለጹ ባለበት ወቅት፣ የእስልምና ምክር ቤቱ ሟቾቹን ለመዘከር የጸሎት ስነስርዓት አድርጓል።
በአብዛኛው ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው መጅሊሱ፣ ያካሄደውን የጸሎት ስነስርአት አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች የለበጣ ነው ሲሉ አልተቀበሉትም።
የእምነቱ አባቶች ከሆኑት መካከል ሼህ አብዱል ሃናን አባ ሜጫ አባ ሸንታ እንደገለጹት ከ53 እስከ 60 የሰው ህይወት የቀጠፈውን አደጋው ተከትሎ መንግስት የሃዘን መግለጫ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የአገሪቱም ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ ለሶስት ቀናት መውለብለብ ነበረበት ብለዋል።
መንግስት ለምን መግለጫ ለማውጣትና ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አልተደረገም ለተባሉት ጥያቄ፣ ሼክ አብዱልሃናን መንግስት ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ካለው ንቀት የመጣ ነው በማለት መልሰዋል
ተጓዞቹ ወደ ሳውድ አረቢያ ከመሄዳቸው በፊት በመጅሊሱ መሪዎች ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸው እንደነበር የእምነቱ አባቶች ይናገራሉ።