እነ ፓስተር ኦሞት አግዋ በድጋሜ ተቀጠሩ

ጥቅምት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት ፓስተር ኦሞት አግዋ ፡ አሽኔ አስቲንና ጀማል ኡመር ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው በድጋሜ ለጥቅምት 25 ተቀጥረዋል።
ቀጠሮ የተሰጠው ሁለተኛው ተከሳሽ አቶ አሽኔ አስቲን የምክር ቤት አባል በመሆናቸው፣ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በመታሰራቸው ፣ ጉዳዩን ለማየት ነው።
እነፓስተር ኦሞት የታሰሩት የውጭ አገር የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በክልሉ ስለሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመነጋገር ኬንያ ናይሮቢ የጠሩትን ስብሰባ ለመሳተፍ ሲጓዙ ነው። መንግስት ተከሳሾቹ የጋምቤላ ህዝብ ነፃ አውጭ አድርጅት አባላት ናቸው ይላል። ይሁን እንጅ ጀማል ኡመር የጋምቤላ ተወላጅ ሳይሆን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ተወላጅ በመሆኑ ፣ ከጋምቤላ ነጻ አውጭ ድርጅት ጋር የሚያገኛኘው ነገር እንደሌለ የአኝዋ ሰርቫይቫል ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ኒይካው ኦቻላ ለኢሳት ተናግረዋል።