የአለማቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች መንግስት በድርቅ ለተጎዱት ዜጎቹ በቂ ገንዘብ እንዲመድብ ጠየቁ

ጥቅምት ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚገኙ 8 ሚሊዮን 200 ሺ ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚሹ፣ በከተማ ውስጥ የሚኖሩ 4 ሚሊዮን ተረጅዎች እንዳሉ በመንግስት እና በአለማቀፍ ድርጅቶች ይፋ ከሆነ በሁዋላ፣ የአለማቀፍ ድርጅቶች መንግስት ለልማት በሚል የመደበውን ገንዘብ የዜጎቹን ነፍስ ለመታገድ እንዲያውለው ጠይቀዋል። እስከሚቀጥለው ታህሳስ ወር ድረስ ምግብ ገዝቶ ለማቅረብ የሚያስፈልገው 12 ቢሊዮን ብር ገደማ ሲሆን፣ መንግስት አብዛኛውን እርዳታ የአለማቀፍ ድርጅቶች እንዲሸፍኑለት ይጠብቃል። ይሁን እንጅ እርዳታ ሰጪ አገራት በተለያዩ አለማቀፋዊ ጉዳዮች በመጠመዳቸው በኢትዮጵያ ለተከሰተው ከፍተኛ የምግብ እጥረት አስፈላጊውን ትኩረት እየሰጡ አይደለም።
በመላው አለም በሚታየው ቀውስ የተነሳ፣ የምእራባዊያን አገራት እርዳታ ከዚህ በፊት እንደሚታየው በፍጥነት የሚቀርብበት እድል እየጠበበ መምጣቱን የሚናገሩት ለጋሽ አገራት፣ የኢህአዴግ መንግስት ለዜጎች ህይወት ቅድሚያ በመስጠት ተጨማሪ ገንዘብ ይመድብ ሲሉ ጠይቀዋል። ሰነዶች እንደሚያሳዩት መንግስት ባለፉት 4 አመታት የስርዓቱን ገጽታ ያሳድጋል በሚል ለክብረ-በአላት እና ለተለያዩ ፖለቲካዊ ስልጠናዎች ፣ አሁን የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የተጠየቀውን ያክል ገንዘብ ወጪ አድርጓል።
ለጋሽ አገራት እንዳስጠነቀቁት በሚቀጥለው አመት የተረጅው ህዝብ ቁጥር 16 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል። በአለም ላይ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች ካልበረዱ ወይም ሌሎች አስቸኳይ እርዳታ የሚሹ ጉዳዮች ካልቀነሱ፣ ከውጭ እርዳታ የማግኘቱ ነገር ቀላል ላይሆን ይችላል።
የኮሎቢያ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች፣ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ የዝናብ እጥረት እንደሚያጋጥመው አዲስ ባወጡት ጥናት የጠቆሙ ሲሆን፣ የዝናብ እጥረቱ በአካባቢው የሚታየውን ግጭት ሊያባብሰው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ጥናቱን ካጠኑት መካከል አንዱ የሆኑት ፒተር ዲ ሜኖካል እንደገለጹት ምንም እንኳ የእርዳታ ድርጅቶች የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዝናብ እንደሚዘንብ ቢተነብዩም፣ ጥናቱ የሚያሳየው ግን ተቃራኒውን ነው ብለዋል። ባለፉት 40 ሺ አመታት የታየውን የአየር ጸባይ መሰረት በማድረግ የተሰራው ጥናት፣ ወደ አየር የሚለቀቀው የካርቦን መጠን ካልቀነሰ፣ አካባቢው እየደረቀ መሄዱን ይቀጥላል ሲሉ ተመራማሪው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በኢትዮጵያ በድርቅ የተጎዳውን ህዝብ ቁጥር በአንድ ወር ልዩነት በእጥፍ አድጎአል ማለቱ በአዲስአበባ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።
ለዘጋቢያችን አስተያየተቸውን የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት በነሀሴ ወር 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ተርቦአል የሚል መግለጫ ከተሰጠ በሃላ፣ በቀጣዩ መስከረም ወር ቁጥሩ ወደ 8 ነጥብ 2 ሚሊየን አድጎአል መባሉ እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል።
መንግስት በአንድ ወር ልዩነት እጥፍ በሚሆን ደረጃ ቁጥሩን ያሳደገው ቀድሞም ትክክለኛ መረጃ ባለመስጠቱ ነው ብለው እንደሚያምኑ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
በየክልሉ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ በድርቁ የተጠቃው ወገን ቁጥር ከዚህም የላቀ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ግብርናው አድጎአል፣ በምግብ እህል ራሳችንን ችለናል በሚባልበት በዚህ ወቅት በአንድ ክረምት የዝናብ መዛባት ይህን ያህል ተረጂ ወገን መታየቱ የገዥውን ፓርቲን የፓሊሲ ውድቀት ያሳያል ማለታቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል።