ጥቅምት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኦሮምያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳ በርጋ ወረዳ 30 ወጣቶች በኦሮምያ ልዩ ሃይሎች በሌሊት ታፍነው መወሰዳቸውን ሂውማን ራይትስ ሊግ ኦፍ ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ ገለጸ።
ድርጅቱ ለኢሳት በላከው መግለጫ አብዛኞቹ የታሰሩት ወጣቶች የናይጀሪያዊው ባለሀብት ንብረት የሆነው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሰራተኞች እና ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቻቸው የሄዱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው። ወጣቶችን በማፈን መመሪያ የሰጠው አቶ ቶሌራ አንበሴ የሚባል የአካባቢ ሹም መሆኑን የሚገልጸው ድርጅቱ፣ ከተያዙት ወጣቶች መካከል ከ20 በላይ የሚሆኑት በኦሮምያ ልዩ ሃይሎች በጽኑ ተደብድበዋል። ህገመንግስታዊ መብታቸው ተጥሶም፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለ3 ቀናት በአዳበርጋ እስር ቤት ታስረዋል።
ወጣቶቹ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ህዝብን በመንግስት ላይ ለአመጽ ማነሳሳት በሚል ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ በዋስ እንዲፈቱ ውሳኔ ቢያስተላልፍም፣ ፖሊስ ግን ለመፍታት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ወጣቶቹን መልሶ ወደ እስር ቤት ወስዷቸዋል። ፍርድ ቤት ከቀረቡት መካከል አንደኛው ከቤተሰቡ ፊት በከፍተኛ ሁኔታ መገረፉንና ባለቤቱና የ16 አመት እህቱ በአንድ ልዩ ሃይል መደፈራቸውን ለዳኞች ተናግሯል። እስረኞቹ የደረሰባቸውን አካላዊ ጉዳት ለፍርድ ቤት ማሳየታቸውንም የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ገልጿል። የኦሮምያ ክልል አስተዳደር የወጣቶች የዋስትና መብት ተጠብቆ እንዲፈቱ እንዲሁም በሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር የፈጸመውና ሰቆቃ ያደረሰው ለፍርድ እንዲቀርብ ድርጅቱ ጠይቋል።
የሰብአዊ መብት ድርጅቱ በእስር ላይ የሚገኙ የ17 ወጣቶችን ስም ዝርዝር አያይዞ አቅርቧል። በበቆጂም ከቤት ማፍረስ ጋር በተያያዘ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶች መያዛቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያመለክታል።