ለመስቀል የታሰበው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት በድጋሚ ተሰረዘ።

መስከረም ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ለአዲስ አመት ዋዜማ በላፍቶ ሊያዘጋጀው የነበረው ኮንሰርት በመሰረዙ በአድናቂዎቹ ዘንድ የፈጠረው ቅሬታ ሳይረሳ ፣ አሁን ደግሞ ለመስቀል በአል ያዘጋጀው ኮንሰርት በድጋሚ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዳይካሄድ መከልከሉን የፎርቺን ሳምንታዊ ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል።
የአዲስ አበባ መስተዳድር የካቢኔ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አቶ ፈለቀ ነጋሽ የ አዲስ አመት ኮንሰርቱ የተሰረዘው በአስተባባሪዎቹ የፈቃድ ጥያቄ የቀረበው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመሆኑ አኳያ አስተዳደሩ ባጋጠመው የስራ መደራረብ ሳቢያ እንደሆነ ለጋዜጣው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አቶ ፈለቀ ይህን ይበሉ እንጂ ለስርአቱ ቅርበት ያላቸው በርካታ አርቲስቶች የአዲስ አመት ኮንሰርታቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲያካሂዱ አስተዳደሩ ትብብር ማድረጉ በስፋት ተዘግቧል።
አስተባባሪዎቹና አድናቂዎቹ ለአዲስ አመቱ ኮንሰርት መሰረዝ በአዲስ አበባ መስተዳድር የተሰጠው ምክንያት አሳማኝ አይደለም በማለት ተቃውሞ እያሰሙ ባሉበት ወቅት ይባስ ብሎ ለመስቀል ያሰናዳው ኮንሰርት በድጋሚ እንዲሰረዝ መደረጉ በአርቲስቱ አድናቂዎች ዘንድ ከፍ ያለ ቁጣና ተቃውሞን ይቀሰቅሳል ተብሎ ይጠበቃል።
እስከ 6 ሺ ሰዎች ይታደሙበታ ተብሎ ተጠብቆ በነበረው በአዲስ ዓመቱ ኮንሰርት አንደኛ ማእረግ ለመታደም የ1 ሺህ 200 ብር እና በመደበኛ ቦታ ሆኖ ለመከታተል የ700 ብር ትኬቶች ከተሸጡ በኋላ እንዲታገድ መደረጉ የ ህዝባዊውን አርቲስት አድናቂዎች ክፉኛ ሲያበሳጭ ሰንብቷል።
ኢህ አዴግ ባለፈው ዓመት አብዮታዊ ዲሞክራሲን ለማስረጽ በሚል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለረዥም ጊዜያት ባካሄደው ስልጠና የቴዎድሮስ ካሳሁንን ሃሳብ መታገል ያስፈልጋል የሚል ጽሁፍ እስከማቅረብ መድረሱ ይታወቃል።