ኢሳት ዜና (መስከረም 14 ፣ 2008)
የግብፅ መንግስት በመገንባት ላይ ያለውን የአባይ ግድብን በልዩ የሳታላይት ቴክኖሎጂ እየተከታተለ እንደሆነ ዛሬ አርብ ይፋ አደረገ።
ሰሞኑን በግብፅ መገናኛ ብዙሃን በግድቡ የውሃ መሙላት ሂደት በግብፅ ላይ የውኋ እጥረት ተፈጥሯል ሲሉ ላቀረቡት ዘገባ ምላሽን የሰጡት የሃገሪቱ ባለስልጣናት፣ በሳተላይት ቴክኖሎጂ በደተረገ ክትትል ግድቡን በውሃ የመሙላት ስራ እንዳልተጀመረ ሊረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
በግብፅ የመስኖ ልማት ሚኒስትር ሆሳም ሆግሃዚ ሃገራቸው በተያዘው ወር አጋማሽ ላይ ባካሄዳቸው ልዩ የሳተላይት ክትትል በግድቡ ላይ ውኋ የመሙላቱ ሂደት እንዳልተጀመረ ሊረጋጥ መቻሉን ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል።
ሃገሪቱ የግድቡን ግንባታ በልዩ ሳተላይት ቴክኖሎጂ ክትትል እንደምታደርግ ስታስታውቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሲካሄድ የቆየውም ድርድር ለጊዜው መቋረጡ ታውቋል።
ኢትዮጵያና ግብፅ የአባይ ግድብ በታችኛው ሀገራት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ እንዲያጠኑ ሁለት አለም አቀፍ ኩባንያዎች ቢቀጥሩም፣ አንደኛው አጥኚ ድርጀት ከጥናቱ ራሱን ማግለሉ ይታወሳል።
የኔዘርላንዱ ኩባንያ የወሰደው እርምጃ ተከትሎም በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል ለአራት አመት ያክል ሲካሄድ የቆየው ድርድር ለጊዜው መቋረጡን የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የግብፅ ባለስልጣናት በበኩላቸው የተቋረጠውን ድርድር በአዲስ መልክ ለማስቀጠል አማራጮች እየታዩ እንደሆነ መግለጻቸውን ዘ-ካይሮ ፖስት ጋዜጣ አስነብቧል።
ሰሞኑን በካይሮና በጊዛ አካባቢ የተፈጠረው የውሃ እጥረትም በሃገሪቱ ለመስኖ ልማት የተደረገውን የውሃ ፍሰት ማሻሻያ ተከትሎ እንደሆነ የግብፅ የመስኖ ልማት ሚኒስትር ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
የግብፅ ባለስልጣናት የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ላቀረቡት የውሃ እጥረት ዘገባም፣ ሃገሪቱ የአባይ ግድብን የውሃ መሙላት ሂደት በልዩ የሳታላይት ቴክኖሎጂ በመከታተል ላይ በመሆኑ የተደበቀ ነገር አይኖርም ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል።
የግብፅ መንግስት የግድቡን ግንባታ በሳተላይት ቴክኖሎጂ መከታተሉ ከኢትዮጵያ ጋር ወደአዲስ ውዝግብ ሊከተው እንደሚችል የተለያዩ አካላት በመግለፅ ላይ ናቸው።