በካዛንችስ በርካታ የንግድ ቤቶች እየፈረሱ ነው

መስከረም ፯ (ሳባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ውስጥ በንግድ እንቅስቃሴያቸው ከሚታወቁት አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው ካዛንችስ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ የንግድ ቤቶች በብዛት የፈረሱ ሲሆን፣ መኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ እንቅስቃሴ በመጀመሩ ነዋሪዎች ስጋት ገብቷቸዋል።
የመንግስት ቤቶችን ተከራይተው ይሰሩ የነበሩ የንግድ ድርጅቶች በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች እንዲሰማሩ ቢደረግም፣ የግል የንግድ ቤት የነበራቸው ግን በካሳ መልክ የተከፈላቸው ገንዘብ በቂ አለመሆኑን እየገለጹ ነው። ተቃውሞአቸውን ቢያሰሙም የሚሰማቸው አላገኙም። በአሁኑ ሰአት ደግሞ መኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ ማስታወቂያዎች እየተነገሩ ሲሆን፣ ነዋሪዎችም በቂ ጊዜና ተገቢው ካሳ ና ተለዋጭ ቤት ሳይሰጠን በአፋጠኝ ውጡ እንባላለን በሚል ስጋት እንደገባቸው ለኢሳት ተናግረዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የመስተዳድሩን ባለስልጣናት ለማናገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።