የውጭ ምንዛሬ ገቢው እቅድ የማይጨበጥ ህልም ነው ተባለ

መስከረም ፯ (ሳባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የወጭ ንግዱን ከ3
ወደ 12 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ መታቀዱ አሁን ሀገሪቱ ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ እጅግ የተጋነነና ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ነው ሲሉ ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ በተካሄደ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ያተኮረ ስብሰባ ላይ የተሳተፉ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ባለሙያው እንደሚሉት በመጀመሪያው የመንግስት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ ላይ ማለትም በ2007 ዓ.ም የወጭ ንግዱን ገቢ 10 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ ታቅዶ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም ከ3 ቢሊየን ዶላር ባላይ ማሳካት አልተቻለም፡፡ ሀገሪቱ የተለመዱትን የግብርና ውጤቶች ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጫትና የመሳሰሉትን ሽጣ ከምታገኘው ገቢ በላይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚገኘው ገቢ እየበለጠ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ ይህ የሬሚታንስ ገቢ ማደጉ በበጎ ጎኑ የሚታይ ቢሆንም አስተማማኝ ባለመሆኑ ለዕቅድ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ይልቅ በተለይ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የኤክስፖርት ምርቶችን በዓይነት፣ በብዛትን በጥራት ማሳደግ ይገባል ያሉት ባለሙያው፣ ኤክስፖርቱን ሙሉ በሙሉ ከግብርና ምርቶች ጥገኝነት ማውጣት እስካልተቻለ ድረስ ሻል ያለ ገቢ ማግኘት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡
መንግስት በመጀመሪያ የዕቅድ ዘመኑ ከወጭ ንግድ አገኘዋለሁ ያለው የገቢ ዕቅድ በመክሸፉ የተለያዩ ፕሮጀክቶቹ እንዲደናቀፉ ምክንያት ሆኖአል ያሉት ባለሙያው፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ አሳታፊ በሆነ መልክ በመንቀሳቀስ የግሉን ዘርፍ ወደመደገፍ መሸጋገር አለበት ብለዋል፡፡ ይህ ባልተሰራበት ሁኔታ ትልቅ ገቢ አልሞ መነሳት የማይተገበር ቅዥት ከመሆኑም በተጨማሪ ከውጭ ንግዱ መውደቅ ጋር ተያይዞ ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ማካሄጃ የውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ስለማይኖር ውድቀቱ የከፋ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
መንግስት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለመቅረፍ በሚል ለሁለተኛ ጊዜ ከግል የውጭ አበዳሪ ባንኮች ለመበደር እንቅስቃሴ ጀምሯል። ቀድም ብሎ በ10 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል 1 ቢሊዮን ዶላር የተበደረ ሲሆን፣ በሁለተኛው ዙር ብድር ምን ያክል ገንዘብ እንደሚበደር እስካሁን የተባለ ነገር የለም።