መስከረም ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መስከረም 16፣ 2008 ዓም በደቡብ ክልል በጌዲዮ ዞን ወናጎ ከተማ ከንግድ ቤት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ውዝግብ አድጎ ወደ ብሄረሰቦች ግጭት በማምራቱ በርካታ ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ የተለያዩ የንግድ ቤቶችም ተዘርፈዋል። የከተማው ባለስልጣኖች ሆን ብለው ቀስቅሰውታል በተባለው በዚህ ግጭት፣ የአንድ ብሄረሰብ አባላት ነን የሚሉ ሰዎች፣ የሌላ አካባቢ ብሄረሰቦች አካባቢያችንን ለቃችሁ ውጡ በማለት ግጭት መፍጠራቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል።
ግጭቱን ማዬሉን ተከትሎ የታጠቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ ከተማው የገቡ ሲሆን፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የከተማው ነዋሪዎችን ይዘው አስረዋል። በርካታ ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተዋል።
ዛሬ መዋል የነበረበት የአካባቢው ገበያ አልዋለም። ሱቆችም ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ሰአት ድረስ አልተከፈቱም። በዞኑ ውስጥ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ግጭቶች እየተሱ ደም አፋሰዋል። የዚህን ዜና ዝርዝር ተጨማሪ መረጃ እንደደሰረን በነገው እለት እናቀርባለን።