ሞላ አስገዶም የሸሸው ሰራዊቱ የአመራር ለውጥ ከመቀየሩ ጋር በተያያዘ ነው ሲሉ ምክትል አዛዡ ተናገሩ

መስከረም ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ታጋይ መኮንን ተስፋዬ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት ድርጅቱ ከሚያዚያ እስከ ነሃሴ በነበሩት ወራት ከታች እስከ ላይ የ7 ዓመታት ግምገማ አድርጓል። የሞላ አመራር “ትህዴንን ወደ ድል አላበቃውም ይቀየር” የሚል ጥያቄ በመላ ሰራዊት አባላት መነሳቱን የተነገሩት ምክትል አዛዡ፣ ሞላ አስጎደም አገርህን አድን ከሚለው አዲስ ጥምረት መመስረት ጋር የተያያዘ አይደለም ብለዋል። ድርጅቱ ከ2 ሺ ዓም ጀምሮ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር በጥምረት ለመስራት ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸው፣ ሞላ የሸሸው ከሰራዊቱ በተነሳው ጥያቄ ፍርሃት ነው ብለዋል።
ሞላ አስጎደም ከወያኔ ጋር ይሰራ ነበር ብሎ መናገር ፍጹም ውሸት ነው የሚሉት ምክትል አዛዡ ፣ የተወሰኑ አባሎቹን ግዳጅ እንሄዳልን ብሎ እንዳደናገራቸው ተናግረዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰራዊት አባላት እንደከዱ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ ትክክል አይደለም የሚሉት አዛዡ፣ ተደናግረው የሄዱት የሰራዊት አባላት 2 በመቶ እንኳን አይሆኑም ብለዋል።
የሻእቢያን ሰራዊት እየደመሰሰ ኢትዮጵያ እንደገባ የተናገረውንም ምክትሉ አጣጥለውታል። ሞላ ወደ ኢትዮጵያ ሲሄድ የተዋጋው ከትሄዴን ሰራዊት ጋር እንጅ ከሻዕቢያ ጦር ጋር አይደሉም ያሉት አዛዡ፣ ተደናግሮ የሄደውን ሰራዊት የመለሰው የትህዴን ጦር እንጅ የሻእቢያ ጦር አለመሆኑን ገልጸዋል። ሞላ ያመለጠውም ለጥቂት ነው ብለዋል። አስቀድሞ መረጃ አልነበራችሁም ለተባለው ደግሞ፣ እኛ የስራ ክፍፍል ስለነበረን፣ ለግዳጅ ሰራዊቱን ተነስ ሲል አልጠረጠርነውም ነበር፣ በሁዋላ መክዳቱ ሲታወቅ ግን የትሄደን ሰራዊት መልሶታል ብለዋል። ከታጋይ መኮንን ተስፋየ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ ከዜናው በሁዋላ እናቀርባለን።
በሌላ በኩል አርበኞች ግንቦት 7 የትህዴንን አቓም በመደገፍ ባወጣው መግለጫ ” የሞላ አስገዶም መክዳት ለአጭር ጊዜ በማህበረሰባችን ላይ የሚፈጥረውን አስጨናቂ ስሜት የምንረዳው ቢሆንም ከዚህ በላይ ልንረዳው የሚገባ ግን በእንዲህ አይነት ከፍተኛ ያመራር ቦታ የነበረ የነበረ ሰው ሙከራ አለመሳካት በእርግጥም የሀገራችን ፖለቲካ እየበሰለ፤ ከግለሰብ አመራሮች ተጽእኖ እየተላቀቀ፤ አዲስ የተባብሮ መታገል አቅጣጫን እያበሰረ እየሄደ መሆኑንና በትናንሽ ሰዎች መግተርተር ይህ ሂደት የማይቀለበስ መሆኑን የሚያመለክት የረጅም ጊዜ ግኝት መሆኑን ነው” ብሎአል።
አርበኞች ግንቦት 7 ይህ ትግል ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሳያደርግ የማይቆምና እንዲያውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለኢትዮጵያ ህዝብም በየጊዜው በሚፈጠሩ እንቅፋቶች ላይ ሳያተኩር ትግሉን በሙሉ ልብ እንዲደግፍ ጥሪ እናደርጋለን ብሎአል።
በሌላ በኩል የዋሽንግተን ዲሲ የጋራ ግብረሃይል ቦሶስት ተቃዋሚ ድርጅቶች መካካል የተፈጠረውን ጥምረት እንደሚደግፍ አስታውቋል። ግብረሃይሉ ባወጣው መግለጫ፣ ” ከሰሜን በረሀ የመጣው የንቅናቄዎች ጥምረት” በደስታ መቀበሉን ገልጿል።
ባለፈው አመት በአገር ቤት ውስጥ የሰላማዊ ትግሉን በህዝባዊ እንቢተኝነት ለማፋፋም 9 የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ለመስራት ተስማምተናል ሲሉ ፈጣን ሁለንተናዊ ድጋፍ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር መስጠቱን ያስታወሰው ህብረቱ፣ ዛሬም ብረት ያነሱ ኢትዮጵያዊ ሀይሎች ለትግል አበርን ሲሉን እኛም ከጎናችሁ አለን የሚል መልእክት እናስተላልፍላቸዋለን ብሎአል። በንቅናቄ ጥምረት ያልተካተቱ ፀረ-ወያኔ ሀይላትም በአሻቸው መንገድ ተባብረው በሁሉም አቅጣጫ የሚነሳውን የጋራ የሀገር አድን ጥሪውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።