መስከረም ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን የባለስልጣናትን ሐብት ምዝገባ ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ እንደተሳነው የኮምሽኑ ምንጮች አጋለጡ፡፡
ለጠ/ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑትን የኮምሽኑ ኮምሽነር ዓሊ ሱሌይማን ትዕዛዝ ተቀብለው ብቻ የሚያስሩና የሚፈቱ በመሆናቸው በአዋጁ መሰረት ለህዝብ ይፋ መደረግ የነበረበት የባለለስጣናት የሐብት ምዝገባ በወቅቱ ለማከናወን ድፍረት ማጣታቸው ታውቆአል፡፡
የሐብት ምዝገባ ሥራን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ ማንኛውም መረጃ ፈላጊ በቀላሉ በኢንተርኔት አማካኝነት መረጃውን እንዲያገኝ የሚያስችለው ቴክኖሎጂ በዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ ፕሮጀክቱ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ኮምሽነሩ ቆራጥ አመራር በመስጠት ሥርዓቱን ሊያስጀምሩት አለመቻላቸው ምንጩ ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት ከ50 ሺህ በላይ ተሿሚዎች፣ ተመራጮችና የመንግስት ሠራተኞች ሃብታቸውን ያስመዘገቡ ሰሆን፣ ይህን መረጃ ግን ኮምሽኑ በተለይ ለመገናኛ ብዙሃን ለመግለጽ ያልቻለው ጉዳዩ የፖለቲካ ውሳኔ በመፈለጉ ተብሎአል፡፡
በሌሎች ሀገራት ሃብት ማሳወቅና ማስመዝገብ የመንግስት አሰራር በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ላይ ተመስርቶ እንዲከናወን የሚያስችል አንዱ የሙስና መከላከያ መንገድ ቢሆንም ፣ ኮምሽኑ ሃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት አቅም በማጣቱ አሰራሩ ተግባራዊ ለማድረግ ተስኖታል።
በስልጣን ላይ ያሉ ከፍተኛ ባለለስልጣናት ከገቢያቸው በላይ ሃብት በማፍራት በተደጋጋሚ ወቀሳ ሲቀርብባቸው ቆይቷል። ግሎባል ፋንይናንሻል ኢንተግሪቲ የተባለው አለማቀፍ ተቋም በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ በ8 አመታት ውስጥ በሙስናና በተለያዩ ምክንያቶች ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከአገር ወጥቷል።