ለትምህርት ጥራቱ መጓደል የዘመቻ ስራዎችና የመምህራን ፍለሰት ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ሆነዋል ሲሉ ባለሙያዎች ተናገሩ

ጷግሜን ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ለልዩ ልዩ ባለሙያዎች ባቀረበው የቀጣይ አምስት አመታት የትምህርት ዕቅድ ውይይት ላይ፣ ባለፉት አመታት የትምህርትን ስራ በትምህርት ባለሙያዎች ሳይሆን ለጉዳዩ ዕውቅና በሌላቸው የፖለቲካ ሰዎች እንዲመራ መደረጉና የዘመቻ ስራ ላይ ማተኮሩ የትምህርቱ ጥራት ለመውደቁ ዋና መንስዔ መሆኑን የስብሰባው ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ባለሙያዎች በአዲስ ዓመት የትምህርት አከፋፈት ላይ በሚደረግ ዘመቻ የሚመዘገቡ አብዛኛው ተማሪዎች ኮታ ለመሙላትና የሐሰት ሪፖርት ለማዘጋጀት ዕድሜያቸው ለትምህርት ያልደረሱ ህጻናትን በማካተት የሚሰራ በመሆኑ በአፈጻጸሙ ላይ ጉድለት መታየቱን ገልጸዋል፡፡
የሌላ ሴክተር ሰራተኖች ሆነው የትምህርት ሽፋንን በተመለከተ ሪፖርት የሚያደርጉበት የአሰራር አግባብ በመኖሩ በሪፖርቱ የሚቀርቡ የተማሪዎች ቁጥር እና በአካል የሚገኙት ተማሪዎች ቁጥር መለያየቱ በርዕሳነ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አስተያየት ሰጪው ይናገራሉ፡፡
በክልል ደረጃ በየዓመቱ የሚታየው የተማሪ ቁጥር መዛባት ምክንያት የሆነው በጉዳዩ ላይ የማይመለከታቸው የጤና ፣ግብርና፣ የአስተዳደር እና ሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች የሚሰሩት የዘመቻ ምዝገባ ነው፡፡የሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች በአንድ ቀን በርካታ ተማሪ አስመዘገቡ በማለት እንዲመሰገኑ ለትምህርት ያልደረሱ ህጻናትን ከመመዝገባቸው ባሻገር፣ የትምህርት ሽፋንን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ከተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር በላይ ሪፖርት የማቅረቡ አሰራር በቀጣዩ ዓመት የትምህርት አመዘጋገብ ዙሪም የሚቀጥል ከሆነ አሁንም ለትምህርቱ ጥራት መጓደል ዋና ምክንት ሆኖ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ለትምህርቱ ጥራት መጓደል እንደ ምክንያት ከሚደመሩት መካከል አንዱ የመምህራን ፍልሰት መሆኑን ተናግረው በተለይ በትግራይ አጎራባች በሆኑት የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ፍልሰቱ በስፋት እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡
የችግሩን ምንጭ ለማወቅ ባደረጉት ክትትል ለፍልሰቱ እንደ ምክንያት የሚቀመጠው በሁለቱ አጎራባች ክልሎች መካከል ያለው የደመዎዝ አከፋፈል ልዩነት መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡በሁለቱ ክልሎች መካከል በተመሳሳይ የአየር ጠባይና የትምህርት ደረጃ የሚሰሩ መምህራንና ባለሙያዎች የሚደረገው የአከፋፈል አድልዎ ባለመወገዱ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች መምህራን በማጣት እስከመዘጋት በመድረሳቸው በርካታ ተማሪዎች የመማር እድል ማጣታቸውን በአስረጂነት አቅርበዋል፡፡የክልሉ መንግስት የመምህራንና ባለሙያዎች ፍልሰት ለትምህርቱ ጥራት መጓደል አንዱ ምክንያት መሆኑን እያወቀ ተገቢውን ዕርምት በመውሰድ ያለውን የአከፋፈል ልዩነት ለማስተካከል ያደረገው ጥረት ዝቅተኛ በመሆኑ አሁንም ፍልሰቱ አላቆመም፡፡
ሌላው ብችግርነት የተነሳው ለአመራሮች የሚሰጠው የትምህርት ዕድል ጉዳይ ሲሆን በወረዳ አመራርነት ለሚያገለግሉ አመራሮች በፍትሃዊነት እንዲማሩ አለመደረጉ በሚመሩት ተቋምና ህዝብ ዙሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎችን በአግባቡ ለመምራት እንደሚስቸግራቸው ገልጸዋል፡፡በአንድ ወረዳ በዓመት ለአንድ አመራር ብቻ የትምህርት ዕድል መሰጠቱ ፍትሃዊ ባለመሆኑ አመራሮችን እንዲማሩ ዕድሉን አለመስጠት በትምህርቱ ጉዞ ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ በማሳደር የትምህርቱን ጥራት በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳው ይናገራሉ፡፡