ጷግሜን ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የማእከላዊ ስታትስቲክስ መስሪያ ቤት ባወጣው ሪፖርት በነሃሴ ወር ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዋጋቸው ጨምሯል። የጭማሪዎች መጠን ከክልል ክልል ሲለያይ አዲስ አበባ ፣ አፋርና ኦሮምያ ከፍተኛ ጭመሪ ታይቶባቸዋል። የምግብ ዋጋ ከአምናው ጋር ሲተያይ 11 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ምግብ ነክ ያልሆኑ ደግሞ በ8 ነጥብ 9 ጭማሪ አሳይተዋል። በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላና አትክልት መረጋጋት ቢያሳይም፣ ስጋ፣ ወተት፣ አይብ፣ እንቁላል ዘይትና ቅባቶች ጭማሪ አሳይተዋል። ከጥራጥሬ ምስር፣ ከቅመማ-ቅመም ደግሞ ያልተፈጨ በርበሬ ዋጋቸው ጨምሯል።
በዋጋ ጭማሪው የተገዱት ክልሎች በተለይ አዲስ አበባ፣ አፋር፣ ኦሮሞና አማራ ሲሆኑ፣ ደቡብ ሶማሊ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪና ትግራይ ከ6 ነጥብ3 እስከ 6 ነጥብ 8 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል። በተለያዩ አገሪቱ አካባቢዎች የሚታየውን ድርቅ ተከትሎ በመጪዎቹ ወራት ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ጭማሪ ይኖራል ተብሎ ተፈርቷል።