ጎጃም ውስጥ በድርቁ ምክንያት በሰውና እንሰሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው

ነኅሴ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአፋር፣ በሶማሊና በሌሎች አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ አድማሱን በማስፋት ጎጃም ውስጥም ተከስትዋል።በድርቁ ጉዳት በርካታ እንሰሳት እየሞቱ መሆኑንና ሰውም ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል። በተለይ ድርቁ በሶማ፣ አራራ፣ እነገ እና ሰንጠርጌ ቀበሌዎች ለበርካታ እንሰሳት ሞት ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር ነዋሪዎችም ለከፍተኛ ችጋር ተጋልጠዋል፡፡
ድርቁ አስከፊ ደረጃ እንደደረሰ መንግስት ማመኑን የገለፁት ነዋሪዎች ነሃሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የእናርጅ እናውጋ የንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም የደብረወርቅ 01 ቀበሌ ሊቀመንበር የድርቁን አስከፊነት በመግለፅ ከህዝቡ ዕርዳታ ማሰባሰባቸውን ስብሰባው ላይ የተገኙት ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡
ከእናርጅ መስቀለ፣ አረጋሚትና ሌሎችም ቀበሌዎች ገለባና ሌሎች ለከብቶች በምግብነት የሚውሉ መኖዎች ተሰባስበው በድርቅ ወደተጠቁት ቀበሌዎች ተልከዋል።
መንግስት ዕርዳታ ለማሰባሰብ የተገደደውና እርዳታ ማሰባሰብ የጀመረው በድርቁ የተጠቁት ቀበሌዎች ነዋሪዎች በዝናብ እጥረት የደረቀውን ሰብላቸውን በመያዝ፣ እንዲሁም በእንሰሳትና ሰው ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በመግለፅ ደብረወርቅ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣታቸውና በተደጋጋሚ አቤቱታ በማቅረባቸው ነው ተብሏል፡፡
በድርቁ የተጠቁት ነዋሪዎች ስለ ድርቁ ለመንግስት ሪፖርት ለማድረግ ወደ አካባቢው ያቀኑ የግብርና ሰራተኞችንና መኪናዎቻቸውን ለተወሰነ ጊዜ በመያዝና በማገት መንግስት መፍትሄ እንዲሰጣቸው በቶሎ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የእናርጅ እናውጋ ወረዳ እስተዳደር ለድርቁ ሁለት መቶ ሽህ ብር መመደቡንና በስብሰባው ወቅትም 28 ሺህ ብር ተዋጥቶ በቆሎ ተገዝቶ እንዲላክላቸው ቢወሰንም እስካሁን እርዳታው ለድርቁ ተጠቂዎች እንዳልደረሳቸውና የአካባቢው ነዋሪዎች የሚበሉት አጥተው እንደተጨነቁና እንሰሳትም በዋሉበት እየቀሩ መሆኑን ገልጸዋል።