አምቡላንሶች ለተለያዩ ፖለቲካዊ አገልግሎት መዋላቸው እንዲቆም ተጠየቀ፡፡

ነኅሴ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለእናቶችና ህጻናት ጤንነት ታስቦ ከተለያዩ ለጋሽ ሃገራት በእርዳታ የተገኙትን አምቡላንሶች ከታሰበላቸው አገልግሎት ውጭ ለተለያዩ ፖለቲካዊ ስራ በመመደብ ሲጠቀሙባቸው እንደነበር በምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ የሚገኙ አንድ የስራ ኃላፊ ገለጹ፡፡
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ኃላፊ እንደተናገሩት የወረዳ አስተዳዳሪዎች በቂ በጀት እንዲመድቡ መመሪያ ቢሰጣቸውም ችላ በማለት አገልግሎት መስጠት የነበረባቸው አምቡላንሶች ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ ችግር ፈጥረውባቸዋል ።
የትራንስፖርት ችግር ባለባቸው ወረዳዎች የሚገኙ አመራሮች አምቡላንሶችን እንደ መደበኛ የስራ መኪና በመጠቀም ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ስራዎችን ያከናውኑባቸዋል ብለዋል።
ባገባደድነው የበጀት ዓመት በጎንጅ፣ወንበርማና ደንበጫ ወረዳዎች የገዢው መንግስት አመራሮች ለመንግስታዊ ስብሰባና ፖለቲካዊ የቅስቀሳ ስራ አምቡላንሶችን በማን አለብኝነት ሲጠቀሙ ነበር።
በአንዳንድ ወረዳዎች እናቶች ለከፍተኛ ህክምና ወደ ባህርዳርና ደብረ ማርቆስ ሆስፒታሎች ሲጓዙ የተጓጓዙበትን የነዳጅ ወጪ ወላድ እናቶች እንዲሸፍኑ በማድረግ ገንዘብ ከአርሶ አደር እናቶች ሲቀበሉ የነበሩ ወረዳዎች አሰራር እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
እነዚህን አይነት ችግሮች ካልቀረፍን በዞኑ በየሳምንቱ የሚገላገሉትን ከአንድ ሽህ በላይ ወላድ እናቶች ህይወት ለማትረፍ የሚደረገውን ስራ ያደናቅፈዋል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ለአምቡላንሶች የተቀጠሩ ሾፌሮች በአንዳንድ ወረዳዎች ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት ካደረሱ በኋላ ለግል ጥቅማቸው ሰው በመጫን የትራንስፖርት ንግድ እንደሚሰሩባቸው ገልጸዋል።
የገዢው መንግስት ባለስልጣናት በተለይ ለምርጫ 2007 በየወረዳዎች የነበሩ አምቡላንሶችን ለቅስቀሳ ስራ በማዋል በርካታ እናቶች በቤት ውስጥ እንዲገላገሉ በማድረግ ለፊስቱላና ለሞት ሲዳርጉ እንደነበር የክልሉ ዘጋቢያችን ገልጿል።