ከአንድ ዓመት በላይ ካለ በቂ መረጃ የታሰሩት የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ተወሰነ

ነኅሴ ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከአንድ ዓመት በላይ በተንዛዛ የፍርድ ቤት ቀጠሮ በእስር ሲማቅቁ የነበሩት አራቱ የፖለቲካ እስረኞችን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች፣ የልደታው ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት፣ ዛሬ ነሃሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ተከሳሾችን አሰናብቷል።
በዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱት የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች አቶ ሀብታሙ አያሌውና ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ አመራር አብርሃ ደስታ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የሸዋስ አሰፋ እንዲሁም 7ኛ ተከሳሽ አብሃም ሰለሞን በነፃ እንዲሰናበቱ ቢባልም፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሺና የሺዋስ አሰፋ ከዚህ ቀደም ችሎት በመድፈር የተፈረደባቸውን ቅጣት ሲያጠናቅቁ ይፈቱ ብሎአል።
አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ከአሁን ቀደም ተከሶበት በነበረውና ከ15 ዓመት በላይ እንደሚያሳስር በሚታወቀው የፀረ ሽብር ህግ አንቀፅ አራት ‹‹ማሴር፣ ማቀድና መተግበር›› ላይ መረጃ ስላልተገኘበት አንቀፁ ተቀይሮ እንዲከላከል ተበይኖበታል፡፡ በዚህ አንቀፅ ላይ ሰዎችን ለግንቦት ሰባት በመመልመል ተግባር ተሰማርቷል በሚል ክስ ቀርቦበታል።
ገዢው ፓርቲ የአሜሪካዊውን ፕሬዚዳንት ባራክ አቦማ ጉብኝት ና የምርጫው መጠናቀቅ ተከትሎ ታዋቂዋን ጸሃፊ መምህርት ርዕዮት አለሙን ጨምሮ የተወሰኑ የዞን ዘጠኝ አባላትን መፍታቱ ይታወሳል።