የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ስደት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ ተነገረ

ኢሳት ዜና (ነሐሴ 8, 2007)

ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ወጣት ከሀገር በመሰደድ ላይ መሆኑ ስጋት እንዳሳደረበት መንግስት አስታወቀ።

የወጣቶቹን ስደት ለመቆጣጠር ጠንካራ የተባሉ ደንቦችና መመሪያዎች ተግባራዊ ቢያደርጉም፣  ከዚህም በፊት ስደት በማይታወቅባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ቁጥሩ ከፍተኛ ወጣት በመሰደድ ላይ እንደሚገኝ በመንግስት የተቋቋመው የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ብሄራዊ ምክር ቤት ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።

በድንበር በኩል ከሚደረጉ ስደተኞች በተጨማሪ በቱሪስት ቪዛ እየተሰደዱ ያሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን እና እገዳ በተጣለባቸው ኳታርና የመን ሀጋዊ ሽፋን እየተሰጣቸው የሚሰደዱ ሰዎች መኖራቸውን የምክር ቢርቱ ሀላፊዎችን ዋቢ በማድረግ በሀገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

ድርጊቱን ለመቆጣጠር የተወሰዱ እርምጃዎችም የተጠበቀውን ውጤት ሳያመጡ መቅረታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ገልጸዋል። በየመን የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጀት የስደተኞች ኮሚሽን ወደ የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር አሳስቦት እንደሚገኝ የድረጅቱ ባለስልጥናት ለኢሳት መግለጻቸውን የሚታወስ ነው።

ጦርነት በቀጠለባት የመን በየወሩ ወደ አራት ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን በስደት እንደሚገቡ የድረጅቱ ባለስልጣናት ለኢሳት መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ድርጅቱ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን መንግስት ሲገልጽ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።

የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) በበኩሉ ከኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እንዲቀንስ ለማድረግ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የማስተማር ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።

ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ከ 200 በላይ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገር መመለሱ የሚታወስ ሲሆን አሁንም ድረስ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከየመን መውጫ አጥተው እንደሚገኙ ገልጿል።