ኢትዮጵያ በኑሮ ደረጃ ስሌት ከ38 የአፍሪካ አገሮች 32ኛ ደረጃ ያዘች
ኢሳት ዜና (ነሓሴ 7, 2007)
ከአፍሪካ የተሻለ የማህበራዊና የኢኮኖሚ አገልግሎት እንዲሁም የዜጎች አጠቃላይ የኑሮ ደረጃቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ተብለው ከተቀመጡት 38 የአህጉሪቱ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ በ32ኛ ደረጃ ላይ መገኘቷን አንድ አለም አቀፍ ተቋም ይፋ ባደረገው አመታዊ ረፖርት ገለጸ።
ሃገሪቱ ለዜጎቻቸው የሚያቀርቡት የጤና፣ የትምህርት፣ ኢኮኖሚያዊና፣ የማህበራዊ አገልግሎቶች በመስፈርትነት በተወሰዱበት በዚሁ ጥናት በአልማዝ ሃብቷ የምትታወቀው ቦትስትዋና ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ለመያዝ ችላለች። ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዚያ፣ ናሚቢያ፣ ጋና፣ አልጀሪያ፣ ማሊ፣ ግብፅና ታንዛኒያ ከ2ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ፣ የማዕከላዊ አፍሪካ ረፐብሊክ ደግሞ በ38ኛ ደረጃ ላይ ተመድባለች።
ኢትዮጵያ በጥናቱ ከተካተቱት 38 ሃገራት መካከል በአጠቃላይ የኢኮኖሚና የማህበራዊ አገልግሎቶች በ32ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፣ በመልካም አስተዳደሯ በ19ኛ ደረጃ ላይ መፈረጇን ጥናቱን ያካሄደው ሌጋተም የተሰኘው ኢንስቲትዩት ገልጿል።
ከአህጉሪቱ በህዝብ ቁጥሯ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ በሰዎች የመብት መከበርና፣ በደህንነት እንዲሁም ለዜጎቿ በምትሰጠው ጥበቃ በ24ኛ እና በ31ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል።
በስራ ፈጠራ እንቅስቃሴዎች ዳግሞ በ30ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፣ በትምህርትና በጤና አቅርቦቷም የ29ኛ እና የ22ኛ ደረጃን እንደያዘች በአመታዊ ጠቋሚ ረፖርቱ ተመልክቷል።
በማህበረሰብ ሃብት በ29ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በደህንነትና፣ ጥበቃ እንዲሁም በስራ ፈጠራ የያዘቻቸው ደረጃዎች በጣም ዝቅተኛ ሆነው መመዝገባቸውን መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገው ተቋም አስታዉቋል።
በ13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ሩዋንዳ አምስት ደረጃዎችን በማሻሻል ከአፍሪካ የተሻለ የለዉጥ ሒደትን ያስመዘገበች ሲሆን፣ ቦትስዋና አንደኛ ደረጃነቷን ማስጠበቅ እንደቻለች ሲኤንኤን ዘግቧል።
በአልማዝ ሃብቷ የምትታወቀው ቦትስዋና፣ የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢ 15ሺ 176 ዶላር የደረሰ ሲሆን በደረጃው የመጨረሻ ሃገር የሆነችው የማዕከላዊ አፍሪካ ረፐብሊክ የዜጎቿ አማካኝ የነፍስ ወከፍ ገቢ 584 ዶላር ብቻ ሆኗል።
የዚሁ ጥናት ሃላፊ የሆኑት ናታን ጋምስተር የአፍሪካ ኢኮኖሚ በእድገት ውስጥ ነው ቢባልም እድገቱ የሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ አለማድረጉን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። በጥናቱ የተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ከኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ላይ መገኘታቸው የታወቀ ሲሆን ኤርትራ በጥናቱ አልተካተተችም።