ለዲያስፖራው የሚሰጠው ትኩረት አገር ቤት ባለው ህዝብ ላይ ቅሬታ እየፈጠረ ነው

ነኅሴ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢህአዴግ መንግስት በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለመያዝ በሚል ስሌት የሚሰጠው የቤት መስሪያ ቦታ፣ ተመሳሳይ ጥያቄ ላቀረቡ ፣ በአገር ውሰጥ ለሚኖሩ ዜጎች ባለመስጠቱ፣ ቅሬታ እየተፈጠረ መሆኑን ዘጋቢአችን ገልጿል። መንግስት የዲያስፖራ ቀን ለማክበር በሚል ሰሞኑን በክልሎችና በአዲስ አበባ እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ በተነሱት ውይይቶች ላይ ይህ የቅሬታ ስሜት መንጸባረቁን ገልጿል።
የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ፣ ለኦሮሞ ተወላጅ የዲያስፖራ አባላት መሬት በፍጥነት እንደሚሰጥ መግለጹ፣ ለአመታት ቤት ለመስራት ቦታ የጠየቁ እና የተከለከሉ ማህበራት አስቆጥቷል።
በተመሳሳይ መንገድም በባህርዳር 4 ሺ 225 የመንግስት ሰራተኞችን ያቀፉ 169 የቤት ስራ ማህበራት 101 ሚሊዮን 40 ሺ ብር በዝግ አካውንት አስቀምጠው፣ ቤት ለመስራት ለአመታት ቢጠባበቁም፣ እስካሁን ሰሚ አጥተው ተቀምተዋል።
የእነዚህ ማህበራት አባላት እንደሚሉት ለዲያስፖራ በአንድ ቀን የሚሰጠው መሬት ፣ ለሃገሬው ነዋሪ ፊቱን አዙሯል።
ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የማህበር አባላት ” የእኛም ገንዘብ፣ የእነሱም ገንዘብ፣ እንዴያውም እነሱ ሌሎች አማራጮች አሉዋቸው፣ እኛ ግን የለንም። መንግስት ዜጋውን ረስቶ ለዲያስፖራ ትኩረት ለምን እንደሚሰጥ አይገባንም።” ብለዋል።
ሌላ የማህበር አባል ደግሞ ” ዲያስፖራ ገንዘብ ልኮልናልና መሬት ስጡን ስንል አይሰጡንም፣ ዲያስፖራው ራሱ መጥቶ ገንዘብ እንዲሰጣቸው፣ ዲያስፖራውን ራሱን በአይናቸው እንዲያዩት ይፈልጋሉ፤ በዚህም የተነሳ ዲያስፖራ ሆነን ለመመለስ ስንል ጅቡቲም ቢሆን እንሂድ እያልን ነው ” ይላሉ።
የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ሃለፊ ዶ/ር አምባቸው መኮንን ሰሞኑን ባቀረቡት ጽሁፍ” ዲያስፖራዎች በየክልል ከተሞች ዲያስፖራ መንደር እየተባለ ለቤት መስሪያ በዳርንጎት መልክ የተሰጣቸውን መሬት በአግባቡ ማልማት የቻሉት ከግማሽ በታች ናቸው ” በማለት ፖሊሲው የገጠውም ፈተና ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ለዲያስፖራ አባላት የሚሰጥ ቦታ እየጠፋ በመምጣቱ፣ መንግስት ክልሎችን ማስገደድ ጀምሯል። ይሁን እንጅ አንዳንድ የክልል ከተሞች፣ በተለይም አዋሳና ናዝሬት ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ እየተቸገሩ ነው።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉና ለዚህ ዘገባ መጠናከር መረጃ የሰጡ የመንግስት አካላት፣ ለዲያስፖራው በለማ ከተማ ላይ ቦታ መስጠቱ የፖሊሲ ችግር መኖሩን በገሃድ የሚያሳይ ነው ሲሉ ይተቻሉ። በለማ ከተማ ላይ መሬት የሚሰጠው በቂ ገንዘብ ለሌለው ነዋሪ እንጅ ፣ ገንዘብ አለው ተብሎ ለሚታመነው ዲያስፖራ መሆን የለብትም፣ ዲያስፖራው ያልለማውን መሬት እንዲያለማ ከከተማ ውጭ ባሉ ገጠራማ ቦታዎች፣ ክፍት መሬት ካለ ተፈልጎ ሊሰጠው ይገባል በማለት ፖሊሲውን እንደሚተቹ ዘጋቢያችን በሪፖርቱ ጠቅሷል።