የፖለቲካ እስረኞች ፍትሕ ሳያገኙ በቀጥሮ እየተንገላቱ ነው

ነኅሴ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አይ ኤስ አይ ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ ለመቃወም መንግስት በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ሰበብ የታሰሩት እነ ማቲያስ መኩሪያ፣ ፖሊስ በጊዜ ቀጠሮ ወቅት ‹‹የቪዲዮ ማስረጃም አለን›› በማለቱና ተከሳሾቹ ‹‹ቪዲዮው ይቅረብልን፣ የቪዲዮ ማስረጃው ለእኛም የመከላከያ ምስክርነት ይጠቅመናል›› ብለው በመጠየቃቸው፣ ፍርድ ቤቱ የቪዲዮ ማስረጃው መቅረብ እንዳለበትና እንደሌለበት ብይን ለመስጠጥ ለዛሬ ነሃሴ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ቢሰጥም ፣ የመናገሻ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት የማይሰራ በመሆኑ ችሎቱ በአራዳ ፍርድ ቤት በተረኛ ዳኛ ታይቷል፡፡ የልደታ ፍርድ ቤትም ‹‹ጉዳዩ አልተመረመረም፡፡›› በሚል ብይን ለመስጠት ለነሃሴ 18 ቀን 2007 ዓ. ቀጠሮ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ቪዲዮው ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሲሰጥ የዛሬው ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ፣ ተከሳሾቹም እየተጉላሉ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አቤት ብለዋል።
2ኛ ተከሳሽ መሳይ ደጉሰው ‹‹ድሃ ቤተሰብ አለን፡፡ ቤተሰቦቻችን መርዳት እንዳንችል እየተጉላላን ነው›› በማለት ችግራቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። በዚሁ የክስ መዝገብ ማቲያስ መኩሪያ ፣ መሳይ ደጉሰው፣ ብሌን መስፍንና ተዋቸው ዳምጤ ሲገኙ ከመሳይ ደጉሰው ውጭ ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡
በተመሳሳይ በአራዳ ፍርድ ቤት የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው አቶ ማሙሸት አማረም ለነሃሴ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ተቀጥሯል፡፡ አቶ ማሙሸት የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም ‹‹ምስክሮቹ ስላልተሟሉና ብዙ መዝገቦችም ስላሉ ምስክርነት መስማት አልቻልንም›› ተብሎአል።
የአንድነት አባልና የሚሊዮኖች ድምፅ ጋዜጣ አምደኛ የነበረው እስማኤል ዳውድ አራዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለነሃሴ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቶበታል።
ፍርድ ቤቱ ‹‹በክረምት ከማይሰሩ የተለያዩ ፍርድ ቤቶች መዝገቦች በመምጣታቸው ምስክርነት መስማት አልቻልንም፡፡ ስራ በዝቶብናል›› በሚል በበርካታ ተከሳሾች ላይ ረዘም ያለ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን ፣ በሰልፉ ሰበብ የታሰሩ ተከሳሾች ፣ በተለይም ሴቶች እና ቤተሰቦቻቸው የተፋጠነ ፍርድ ልናገኝ አልቻልንም፣ በሚል ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ ሲያለቅሱ ተስተውለዋል ሲል ነገረ – ኢትዮጵያ ዘግቧል።