ነኅሴ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሽብር ወንጀል ተከሶ ቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኘው አበበ ካሴ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመበት ታወቀ
አበበ ካሴ፣ በማእከላዊ እስር ቤት የሁሉም ጣቶቹ ጥፍሮች ተነቅለው፣ በዘር ፍሬው እና በመላ አካላቱ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበት መረጃ ለማውጣት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ በመጨረሻ ቂሊንጦ እስር ቤት ከተወረወረ በሁዋላ፣ የደረሰበትን ችግር ሁሉ ዘርዝሮ በመጻፍ ለመገናኛ ብዙሃን በድብቅ እንዲደርስ ማድረጉን ተከትሎ ከፍተኛ ጫና ደርሶበታል።
ሀምሌ 27/2007 ዓ.ም ቂሊንጦ እስር ቤት ጨለማ ቤት ታስሮ ከፍተኛ ድብደባ የተፈጸመበት አበበ፣ ሀምሌ 27/2007 ዓ.ም በእሱ የክስ መዝገብ ለተከሰሱ ሁለት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር ሆኖ መቅረብ የነበረበት ቢሆንም፣ በወቅቱ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እሱ እንዳይቀርብ ተደርጓል፡፡
አበበ ችሎት ላይ በሚቀርብበት ወቅት የሚደርስበትን በደልና እንዲሁም ስርዓቱ የሚፈፅመውን ግፍ በተደጋጋሚ ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፣ በሀምሌ 27/2007 ዓ.ም ችሎት ላይም ልትናገር እንደሆነ አውቀናል በሚል ድብደባ እንደተፈጸመበት የኢሳት ምንቾች ገልጸዋል።
የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች የተፈፀመበትን ድብደባ በሚዲያ በማሳወቁ እንደተበሳጩ የታወቀ ሲሆን፣ ድብደባ ሲፈጽሙበትም ‹‹ከውጭ እነሱ፣ ከውስጥ አንተ አስቸግረሃል፡፡›› ብለውታል፡፡ ‹‹ከሚፈፅሙብኝ ድብደባ በተጨማሪ ችሎት ቀርቤ ሀሳቤን እንዳልገልጽ ነው ያስቀሩኝ›› ያለው አቶ አበበ፣ ሀምሌ 28/2007 ዓ.ም ተከሳሾቹና ተመልካች በሌለበት ልደታ ፍርድ ቤት ቀርቦ የመከላከያ ምስክርነት ቃሉን እንደሰጠም ታውቋል።