ኢሳት (ነሐሴ 4፣ 2007 ዓም)
200 የሚጠጉ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በማላዊ እስር ቤቶች የጤንነታቸው ሁኔታ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አንድ አለምአቀፍ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ገለጠ።
ኢትዮጵያዉያኑ ከባለፈው አመት ታህሳስ ወር ጀምሮ በማላዊ መዲና ሊሎንግዌ በእስር ላይ መሆናቸውን ዶክተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ (Doctors Without Borders) የተሰኘ የፈረንሳይ ድርጀት አስታውቋል።
በማላዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተወካይ የሆኑት ኒኮሌት ጃክሰን ስደተኛ ኢትዮጵያኑ በተጨናነቀ ሁኔታ በእስር ላይ መሆናቸው የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ እንዲሆን ማድረጉን ኒዉስ 24 ከተሰኘ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
ዶክተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ (Doctors Without Borders) የተሰኘው ግብረ-ሰናይ ድረጀት ወደ 200 ለሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የህክምና አገልግሎት ሲያደርግ ቢቆይም የአብዛኞቹ ጤንነት መሻሻል አለማሳየቱን ሃላፊዋ ገልጸዋል።
800 ብቻ እስረኞን መያዝ በሚችል አንድ እስር ቤት 2 ሺህ አራት መቶ የሚጠጉ እስረኞች በተጨናነቀ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ጋዜጣው በዘገባው አመልክቷል።
በህገወጥ መንገድ ወደማላዊ ገብታችኋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉት ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች መቼ ከእስር ቤቱ እንደሚወጡ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩን የግብረ-ሰናይ ድርጀቱ ሃላፊዎች አስረድተዋል።
የስደተኞቹን ሁኔታ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ እስረኞቹን ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከማላዊ መንግስት ጋር ድርድር እያካሄደ መሆኑ ታውቋል።