ኢሳት ዜና (ነሐሴ 4፣ 2007)
ሰሞኑን በአፋር ክልል የተከሰተው ድርቅ ተባብሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቁምና የቤት እንስሳት መሞታቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ በክልሉ በክረምት ወቅት የሚጠበቀው ዝናብ በሚፈለገው መጠን ባለመዝነቡ ምክንያት ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን በመግለፅ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ከአዲስ አበባ ወደ አፋር ክልል መዲና በሚወስደው ዋናው አስፋል መንገድ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቁምና የቤት እንስሳት በድርቁ ምክንያት ሞተው መመልከቱን አቶ አዳሙ ከበደ የተባሉ ሹፌር ለአሶሼትድ ፕሬስ ገልጸዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያና በሰሜን ምስራቅ አካባቢ ባሉ በርካታ ዞኖችና ቀበሌዎች ድርቁ አስከፊ ጉዳት በማድረስ ላይ መሆኑን የዜና ወኪሉ የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ ዘገባው አመልክቷል።
የአፋር የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የዝናብ እጥረቱን ተከትሎ የተከሰተው ድርቅ አፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጠው የነዋሪዎችን ህይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።
የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በበርካታ የኦሮሚያ፣ አፋርና፣ ሶማሊያ ክልሎች በሚገኙ ዞኖች ከፍተኛ የዝናብ እጥረት ማጋጠሙንና የሰብል እርሻ ስራ መስተጓጎሉን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ በቂ የምግብ ክምችት መኖሩን አስታውቆ፣ ገበሬዎቹ ድርቅ ቻይ የሆኑና በቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲዘሩ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን እያቅረበ እንደሚገኝ ገልጿል።
የሚኒስትሩ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ወንድሙ ፍላቴ በሃገሪቱ የምግብ እጥረት እንዳይከሰት ለማድረግ ከውጭ ሃገር በቂ ክምችት ወደ ሃገር ውስጥ ሲገባ መቆየቱን ለአሶሺየትድ ፕሬስ አስረድተዋል።
በተያዘው የክረምት ወቅት ያጋጠመውን የዝናብ እጥረት ትከትሎ በአፋር ክልል የተከሰተው ድርቅ በሌሎች አካባቢዎችም ይከሰታል የሚል ስጋት በነዋሪዎች ዘንድ መኖሩን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የተለያዮ አካላት በአፋር ክልል ስላለው ድርቅ የተለያዩ መረጃዎችን ይፋ በማድረግ ላይ ቢሆኑም፣ መንግስት እስከ አሁን ድረስ በክልሉ ስለደረሰው ጉዳት የገለጸው ነገር የለም።