አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከህወሃት የደህንነት አባላት ጋር መስማማት አልቻሉም።

ነኅሴ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ ኢህአዴግ ባደረገው ግምገማ ፣ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እርሳቸውንና ቤተመንግስቱን ከሚጠብቁ የደህንነት ሃይሎች ጋር ተስማማተው መስራት አልቻሉም የሚል ትችት ከቀረበባቸው በሁዋላ፣ ግንኙነቱ ወደ ባሰ ደረጃ መውረዱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
አቶ ሃይለማርያም “በቤተሰቦቼና እና በእኔ ላይ በሚደረገው አላግባብ ክትትል ተሰላችቻለሁ” የሚል ንግግር በሁለተኛው ዙር የኢህአዴግ ሂስ እና ግለ ሂስ የአቋም ግምገማ ላይ ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት ጉዳይ አማካሪ አቶ ፀጋየ በርሄ እና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ዶ/ር ደብረ ፅዩን ፣ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። አቶ ሃይለማርያም ” መለስ ገ/እግዚአብሄርን ጨምሮ ሌሎች 5 የደህንነት አባላትን በእኔ ጥበቃ ውስጥ አልፈልጋቸውም” ቢሉም ሰሚ አላገኙም።
የኢህአዴግ አመራር፣ ለመሪዎች ጥበቃ የሚመረጡ የደህንነት አባላት በተጠባቂዎች ምርጫ የሚካሄድ አለመሆኑን በመናገር አቶ ሃይለማርያም፣ ተግባብተው እንዲሰሩ መክረዋል።
ይሁን እንጅ በጠቅላይ ሚንስትሩ እና በ ጠ/ሚኒስትሩ የደህንነት ጉዳይ ዋና ሃላፊ በመለስ ገ/እግዚአብሄር መካከል የሚታየው አለመግባባት እየጨመረ እንጅ እየተሻሻለ አለመሄዱን ምንጮች ገልጸዋል።