ነኅሴ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስአበባ ዓለም አቀፍ መስፈርት የሚያሟሉ ሆቴሎችን ደረጃ ለመመደብ በተካሄደው ጥናት 98 ያህል ሆቴሎች ከደረጃ በታች ሆነው መገኘታቸው ይፋ ሆኗል።
በዓለም አቀፉ ቱሪዝም ድርጅት ከፍተኛ ባለሙያዎች ተጠንቶ ባለፈው ቅዳሜ ይፋ በተደረገው ውጤት መሠረት ለውድድር ከቀረቡት 136 ያህል ሆቴሎች ደረጃ ማግኘት የቻሉት 38 ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት ባለ5 ኮከብ ያገኙት 3 ሆቴሎች፣ ባለ4 ኮከብ 11 ሆቴሎች፣ ባለሶስት ኮከብ 13 ሆቴሎች፣ ባለሁለት ኮከብ 10 ሆቴሎች፣ ባለአንድ ኮከብ አንድ ሆቴል ብቻ ናቸው።
ባለፈው ቅዳሜ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አዳራሽ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ደረጃ የተሰጣቸው የሆቴሎቹ ዝርዝር በቅዳሜው መግለጫ ላይ አልተገለጸም፡፡ ሚኒስቴሩ ደረጃ ያገኙና ያላገኙ ሆቴሎችን ዝርዝር በቅርቡ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን ፣ ዝርዝሩ ከተነገረ በሃላ ሆቴሎቹ ያገኙትን ደረጃ በግልጽ ቦታ እንዲለጥፉ ይገደዳሉ፡፡ ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት ካስቀመጣቸው መመዘኛዎች መካካል የሆቴሉ የምግብ ጥራት፣አገልግሎት አሰጣጥ፣ ንጽህና፣ የባለሙያዎች ብቃት፣ እና ተያያዥ አግልግሎቶች ማለትም እንደተሸከርካሪ ማቆሚያ፣አረንጓዴ ቦታዎች፣ የጥበቃ አገልግሎቶች ይገኙበታል፡፡
በአዲስአበባ የሚገኙ ሆቴሎች ግንባታቸው ከመከናወኑ በፊት ለሆቴል አገልግሎት ታቅደው በዚያው መሰረት ግንባታቸው የተከናወኑ ሆቴሎች ቁጥራቸው አነስተኛ ሲሆን ፣ አብዛኛዎቹ ለሁለገብ ወይም ለቢሮ አገልግሎት ታስበው በመጨረሻ
ዲዛይናቸው ተቀይሮ ወደሆቴል የተዛወሩ በመሆናቸው በበርካታ ችግሮች እንዲተበተቡ አድርጓቸዋል፡፡ የሆቴሎቹ ግንባታ ከተጠናቀቀም በሃላ ያለምንም መስፈርት ለዓመታት ራሳቸው ለራሳቸው ባለአራትና አምስት ኮከብ ደረጃ በመስጠት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ መሆናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያለው ምንጫችን ይገልጻሉ። ብዙዎቹ የሆቴል ባለሃብቶች ለዘርፉ የተሰጠውን ከቀረጥ ነጻ ዕቃ የማስገቢ ማበረታቻ ስቧቸው የገቡ በመሆናቸው
ለዘርፉ ካላቸው የዕውቀት ማነስ ጋር በተያያዘ ከደረጃ በታች መሆናቸው የሚጠበቅ መሆኑን አስተየያት ሰጪዎች ይናገራሉ።