በደብረዘይት በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቀሉ

ሐምሌ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የከተማው ባለስልጣናት ትናንት በቀበሌ 01 በድንገት በጀመሩት የቤት ማፍረስ እንቅስቃሴ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቤት አልባ ሆነዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኦሮምያ ፖሊስ በአካባቢው ሰፍሮ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከመቆጣጠር አልፎ ፣ ህጻናትንና ወጣቶችን እየደበደቡ አፍሰው ማሰራቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል። ብዙዎች በእለቱ በጣለው ዝናብ የቤት እቃዎቻቸው ተበላሽቶባቸዋል። ” ቤታችን ለምን ይፈርሳል ብለዉ የጠየቁ ዜጎች መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ ይስሩላችሁ” የሚል መልስ ተሰጥቷቸዋል ቤት የማፍረሱ እንቅስቃሴ ዛሬም ቀጥሎአል።
በመላ አገሪቱ በሚካሄደው በህገወጥ ስም የሚፈርሱ ቤቶች ዜጎችን ለስቃይ እየዳረጉ ነው። ስርአቱ ዜጎች ህጋዊ ቤቶችን እንዲያገኙ ወይም በህጋዊ ሁኔታ ቦታዎችን ወስደው እንዲሰሩ ባለማድረጉ፣ ነዋሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት የጨረቃ ቤቶችን ሲገነቡ ቆይተዋል። በአብዛኖቹ አካባቢዎች ነዋሪዎች ቤቶቹን ከሰሩ በሁዋላ መብራት እና ውሃ የገባላቸው ሲሆን፣ ለመንግስትም ግብር ሲከፍሉ ቆይተዋል። የስርአቱ ባለስልጣናት በድንገት እየተነሱ ለአመታት የኖሩ ነዋሪዎችን ማፈናቀላቸው፣ በልማት ስም ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ ቀውስ እየተፈጠረ ነው በማለት ዘጋቢያችን ትዝብቱን አስፍሯል።