በአርባምንጭ አንድ ወጣት ሰቆቃ ተፈጸመበት

ሐምሌ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ወጣት ባንተወሰን አበበ ያልምንም ተጨባጭ መረጃ ሃምሌ 6፣ 2007 ዓም ከታሰረ በሁዋላ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ እንደተፈጸመበት ለኢሳት ተናግሯል። ባንተወሰን ከተያዘ ከሁለት ቀናት በሁዋላ ፍርድ ቤት ቢቀርብም፣ ዳኛው በዋስ እንዲለቀቅ ማዘዛቸውን ይሁን እንጅ ፣ ፖሊስ አልፈታም በማለት ፣ ሃምሌ 17 ከምሽቱ 12፣ 40 ላይ ከእስር ቤት አውጥተው ሰቆቃ ( ቶርቸር) እንደፈጸሙበት ገልጿል። ውሃ እየተደፋበት መደብደቡን እንዲሁም በኤልክትሪክ መቃጠሉን የተናገረው ባንተወሰን፣ ጉንጮና ኩላሊቱ አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።
በድበደባው ራሱን ስቶ እንደነበር የሚናገረው ወጣቱ፣ እየደከምኩ ስሄድ መልሰው ወደ ክፍሌ ወሰደውኝ በእስረኞች እርዳታ ተርፌአለሁ ብሎአል። በእስር ቤት ውስጥ ያደረሱብኝ ግፍ ፣ ከተፈታሁ በሁዋላ ህይወቴን እንድጠላውና መኖር እንደሌለብኝ ውስጤ እየነገረኝ ነው ሲል ተናግሯል በድብደባው ወቅት ለግንቦት7 ወጣቶችን እየመለመለ እንደሚልክና ኔትወርኩን እንዲጋልጥ፣ የተደበቀው መሳሪያ እንዳለና እንዲያመጣ መጠየቁን ገልጿል። “‘አንተንም ቤተሰብህም አንለቅህም’ ስላሉኝ ከመሞቴ በፊት አለም ይወቅልኝ በማለት ለመናገር ደፍሬአለሁ” ሲል ጭንቀቱን ገልጿል። በመጨረሻም በ3 ሺ ብር ዋስ መፈታቱን ወጣቱ ተናግሯል።