ሐምሌ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዚህ አመት በአገሪቱ የታየው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እየከፋ በመሄዱ፣ በጥቁር ገበያ እና በህገወጥ መንገድ የሚደረገው የዶላር ዝውውር መድራቱን ዘጋቢአችን ገልጿል።
ከውጭ ንግድ ጋር በተያያዘ ስራቸውን የሚሰሩ ነጋዴዎች ዶላር እንደልባቸው ለማግኘት ባለመቻላቸው፣ ዶላርን ከጥቁር ገበያና ከባንኮች በልዩ ሁኔታና በውድ ዋጋ ለመግዛት እየተገደዱ ነው። የተወሰነ መጠን ዶላር ለማግኘት ለባንክ ባለስልጣናት ኮሚሽን መክፈል ግዴታ መሆኑን ነጋዴዎች እየተናገሩ መሆኑን ዘጋቢያችን ተናግሯል።
አገሪቱ ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ይልቅ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ የተሻለ ገቢ እያስገኘ ነው። አገሪቱ በቅርቡ ከግል አበዳሪ ተቋማት 1 ቢሊዮን ዶላር መበደሯ ይታወቃል።