በባህር ዳር ከተማ የተከሰተው የነዳጅ እጥረት ህዝቡን እያማረረ ነው

ሐምሌ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በነዳጅ እጥረት ምክንያት የየዕለቱን ስራ ለመስራት የባጃጅ ኮንትራት በመያዝ ለአላስፈላጊ ወጭ መዳረጋቸውን የሚገልጹት የከተማ ነዋሪዎች ጠዋትእና ማታ በሚኖረው ረዣዢም ሰልፍ ምክንያት ስራ ቦታቸው በሰዓት ለመውጣትና ለመግባት መቸገራቸውን ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በነዳጁ መጥፋት ለረዢም ሰዓታት ስራ መፍታታቸው በኑሯቸው ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የሚናገሩት በከተማዋ የሚገኙ የባጃጅ አሽከርካሪዎች የነዳጅ ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ በተደጋጋሚ የነዳጅ እጥረት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ የነዳጅ ማደያዎች ቀኑን ሙሉ ተራ በመጠበቅ እንዳሳለፉ የሚናገሩት አሽከርካሪዎች ከሳምንት በላይ ነዳጅ በማጣት በየቀኑ ስራ ፈተው እንደሚውሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡በጥቁር ገበያ ከስምንት ብር በላይ በእያንዳንዱ ሊትር በመጨመር በሃያ አምስት ብር በመግዛት ቢንቀሳቀሱም በዚህ አይነት ሊዘልቁ አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በከተማው የንግድና ትራንስፖርት መምሪያ ሃላፊዎችም ለጥያቄያችን ተገቢውን ምላሽ አልሰጡንም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች ሁል ጊዜም ስብሰባ ላይ ነን በማለት እንደማያስተናግዷቸው ተናግረዋል፡፡ ያለ ስራ ቁመው ቢውሉም ለባለሃብቶች የእለት ገቢ መስጠት እንዳለባቸው የሚናገሩት አሽከርካሪዎች፤በየእለቱ ገቢ ካላገኙ ቤተሰብን ለመምራትና ራሳቸውም በልተው ለማደር እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡
በከተማው የሚገኙ ማደያዎች በርካታ ቢሆኑም በሁሉም ማደያዎች ቤንዚን የለም በማለት ለስራቸው እንቅፋት እንደሆኑባቸው የሚናገሩት አሽከርካሪዎች፣ ምሳ ለመብላት የሚቸገሩ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡