ፕሬዚዳንት ኦባማ በሰላም አስከባሪ ስም ተሸፍኖ የቀረበውን ተቃዋሚዎችን በሽብርተኝነት የሚፈርጀውን ጥያቄ ሳይቀበሉት ቀሩ

ሐምሌ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፕ/ት ባራክ ኦባማ ከአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በውጭ አገር በተለይም በአሜሪካ የተቀመጠ ተቃዋሚ ድርጅት በሽብረተኝነት እንዲፈረጅ የቀረበውን ጥያቄ ሳይቀበሉት ቀርተዋል። አቶ ሃይለማርያም ” ሽብርተኝነትን በመዋጋት እንዲሁም ሰራዊታችንን በጸጥታ አስከባሪነት ስም ለመላክ የማንችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰን ነው” የሚል ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን፣ ለዚህም የሰጡት ምክንያት “በኤርትራ በኩል የሚነሱ ታጣቂ ሃይሎች የፈጠሩትን ተጽኖ ለመቋቋም ሰራዊታችንን ለማውጣት ስለምንገደድ ነው” የሚል ነው።
ፕሬዚዳንቱ፣ የአቶ ሃይለማርያምን ማስፈራሪያና ማንገራገሪያ ባለመቀበል፣ በተቃራኒው የአገር ቤት ተቃዋሚዎች ሌሎች አማራጮችን እንዲመርጡ የሚገደዱት በአገር ውስጥ ያለው ስርአት ሁሉን አቀፍ ባለመሆኑ ነው ያሉ ሲሆን፣ ስርአቱ አስፈላጊውን የዲሞክራሲ ለውጥ ካላደረገ በስተቀር፣ ዘላቂ የሆነ እድገትና ልማት ማምጣት አይችልም ብለዋል። የጋዜጠኞችን መታሰር እንዲሁም ያለፈውን ምርጫ በማንሳት አገዛዙን አጥብቀው መንቀፍ ሲጀምሩ፣ አቶ ሃይለማርያም ጥያቄያቸውን ወደ ጎን ትተው የቀረበውን ትችት መቀበላቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ባራክ ኦባማ የአፍሪካ መሪዎችን መገሰጻቸው በአዎንታዊ ጎኑ እንደሚያየው መድረክ ዛሬ በበተነው መግለጫ አስታውቋል።
በአፍሪካ ሕብረት ዋና ጽ/ቤት በኔልሰን ማንዴላ መሰብሰቢያ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ከ2 ሺ 500 እስከ 3 ሺ
ለሚገመቱ ተሰብሳቢዎች ኦባማ ባሰሙት ንግግር፣ ጥቂት የአፍሪካ ሀገሮች በቅርቡ ተስፋ ሰጪ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ያካሄዱ ቢሆንም አንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች መሪዎች ራሳቸውን ከሕገመንግሥት በላይ በመቁጠር ከሕግ ውጭ በስልጣን ላይ ለመቆየትና በሀገሮቻቸው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዳይኖር እንቅፋት በመሆን ሕግንና የሕዝቡን መብት በመጣስ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፣ እነዚህ መሪዎች ከዚህ ዓይነቱ ፀረ- ዴሞክራሲያዊ ተግባራት ሊታቀቡ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ፕረዘዳንት ኦባማ ዴሞክራሲ በየወቅቱ ምርጫዎችን በማካሄድ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ነፃ ተሳትፎ በማረጋገጥ፣ ድምፁንም ባለማክበርና የሥልጣን ባለቤትነቱን በትክክል ተግባራዊ በማድረግ እውን ሊሆን እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሁኔታ አስመልክተው ሲናገሩም እኤአ በ2015 (በ2007 ዓ ም) በኢትዮጵያ የተካሄደው ምርጫ ያለብጥብጥ መጠናቀቁ ቢያስደስታቸውም፣ በሀገሪቱ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትና በጋዜጠኞች ላይ እየተፈጸሙ ያሉት እስራቶችና ወከባዎች፣ እንዲሁም ነፃ የሲቭክ ማሕበራት እንዳይኖሩ የሚፈጸሙት ጫናዎችና አፈናዎች እንደሚያሳስቡዋቸው፣ የእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ማግኘትም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ስለሆኑ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚ/ር አቶ ኃይለማሪም ደሳለኝ ጋር ባደረጉት ውይይት መናገራቸውንና ጠቅላይ ሚ/ሩም ለወደፊቱ ተገቢው ማስተካከያዎች እንደሚደረጉ እንደገለጹላቸው አስረድተዋል፡፡
የአፍሪካ መሪዎች የስልጣን ገደብ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ አፍሪካውያን እንደ ሌሎች አህጉራት ህዝቦች እኩል የሚያደርጉዋቸው አለማቀፍ መብቶቻቸው ሊከበሩላቸው እንደሚገባ ፣ መብቶቻቸው ሲጣሱ ሁሉም አለማት መጮህ እንዳለበት በንግግራቸው አስምረውበታል።
በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ዘርፎች አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ዕድገት እያሳየች መሆኑዋን የገለጹት ፕሬዘዳንት ኦባማ፣ በአህጉሪቷ እየተንሰራፋ የሚገኘው ሙስና ግን ለዕድገቱዋ ካንሰር (ነቀርሳ) ስለሆነ መወገድ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምባገነን መንግስታት ስር ለሚዳክሩ ህዝቦች መልእክት ሲያስተላልፉ በአዳራሹ ይሰማ የነበረው ጭብጨባ፣ በአዳራሹ የነበሩትን ጋዜጠኞች አስገርሟል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ኒኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ በበኩላቸው በዚሁ ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር
አፍሪካዊያን ችግሮቻቸውን ተባብረው ለመፍታትና ለዓለም ሰላም መከበርም ጠንካራ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው
አህጉሪቷ በተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ም/ቤት ውስጥ ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት አቦማ እንኳንም ኢትዮጵያን ጎበኙ የሚሉ አስተያየቶች በስፋት እየቀረቡ ሲሆን፣ ጉብኝቱ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የመብት አፈና በአለም መገናኛ እንዲሸፈን አድርጎታል ይላሉ። ታላላቅ የሚባሉት አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ስለሚታየው የሰብአዊ መብት ጥሰትና አፈና ዘገባዎችን ይዘው ወጥተዋል።