ሐምሌ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በ12ኛው የፍትህ ሚኒስቴርና የክልል ፍትህ ቢሮዎች የጋራ መድረክ ላይ እንደተነገረው በበጀት አመቱ የተቋረጡ መዝገቦች በሙሉ ኦዲት ተደርገው ሲጣሩ፣ በአጠቃላይ የፍርድ ቤት መዝገቦች የተዘጉት በክራይ ሰብሳቢነት፣በዝምድናና በተያያዙ የገንዘብ ጉዳዮች መሆኑን የስብሰባው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል የፍትህ ቢሮ ኃላፊ በክልላቸው በስፋት በሚታየው ህገወጥ የሰወች ዝውውር ላይ በሰጡት አስተያየት ፣ በርካታ ወጣቶች ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲኮበልሉ የሚያግዙ የኃይማኖት መሪዎችና የፍትህ አካላት ተሳትፎ ከፍተኛ ደረጃ እንደነበር ገልጸዋል፡፡እንደ ኃላፊው አገላለጽ በሐዲያና ከምባታ አካባቢ ያሉ አመራሮች በሙሉ ዘመዶቻቸውን ወደ ስደት መላካቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
አምባሳደር ተስፋየ ሀቢሶ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ሆነው በተሾሙበት ወቅት በርካታ የደቡብ አካባቢ ተወላጆች ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲወጡ መደረጋቸውንም በውይይቱ የተሳተፉ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
አምባሳደር ተስፋየ ሃቢሶ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር በነበሩበት ወቅት ከኢትዮጵያውያን ገንዘብ በመቀበል ሰዎችን ወደ ደቡብ አፍሪካ ያሻግራሉ የሚል ትችት ይቀርብባቸው ነበር።