በአዲስ አበባ የሲኤምሲ አካባቢ ነዋሪዎች በድጋሚ ልንፈናቀል ነው አሉ

ሐምሌ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ሲኤምሲ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የሚኖሩ 43 አባወራዎች ከ200 በላይ ቤተሰቦች ቀደም ብለው ይኖሩበት የነበረውን ቀያቸውን በልማት ምክንያት ለቀው በተጠቀሰው ወረዳ እየኖሩ ቢሆንም በመንገድ ግንባታ ምክንያት ሕገወጥ ገንቢዎችን ለማዳን ተብሎ እነሱ በድጋሚ ሊፈናቀሉ መሆኑን በመጥቀስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲታደጓቸው የተማፅኖ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡
ይመለከታቸዋል ላሏቸው የመንግስት ተቋማት በሙሉ የድረሱልን ጥሪ በማድረግ ላይ የሚገኙት ዳግም የመፈናቀል አደጋ ውስጥ መሆናቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎች ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የተፈናቀሉ ናቸው፡፡በ1985 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል ግንባታ ምክንያት የተነሱ የፍል ውኃ አካባቢ ነዋሪዎች፣ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በመልሶ ማልማት ምክንያት ከካዛንቺስ የቀድሞ ቀበሌ 30 እና 31 ኢንተርኮንቴኔንታል ሆቴልና በአካባቢው የነበሩ፣ከመገናኛ ዲያስፖራ አደባባይና በሸራተን ማስፋፊያ ምክንያት የተፈናቀሉ ናቸው፡፡
ነዋሪዎቹ ከወጣት እስከ 100 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አዛውንቶች ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ እስከ አሥር ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ በማውጣት የገነቡት ሆቴል ሙሉ በሙሉ እንደሚፈርስ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡ከአሥር ዓመታት በላይ የኖሩበት ቤትና ድርጅት ያለምንም ማስጠንቀቂያ በ15 እና በሦስት ቀናት ውስጥ እንደሚፈርስ በድንገት መናገር ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ ከ20 በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድርን ሆቴል በድንገት ማፍረስ ዜጎችን ሥራ አጥ ከማድረጉም በላይ ምን ያህል ቤተሰቦችን ሊጎዳ እንደሚችልም ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሕገወጥ ግንባታዎችን ለማትረፍ ሁለትና ሦስት ዲዛይኖች እየተቀየሩ በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ አባወራና እማ ወራዎችን በድጋሚ ለማፈናቀል መሯሯጡ ስለበዛባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ለሌሎች ለሚመለከታቸው የፌደራል መንግሥት ተቋማት መሪዎች በማመልከት እንዲታደጓቸው እየለመኑ መሆኑን በድጋሚ ተናግረዋል፡፡
አቶ በዛብህ ባህሩ የ100 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ ከቀበሌ 30 እና 31 ካዛንቺስ ኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ከተገነባበት አካባቢ ተፈናቅለው ወደ ሲኤምሲ መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡የዘጠኝ ልጆች አባት መሆናቸውንና ከ50 ዓመታት በላይ ከኖሩበት ቀያቸው የተፈናቀሉት ከተማ ማደግ ካለበት የዕድገቱ ደጋፊ መሆን እንዳለባቸው በማመናቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡አሁን ግን አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በድጋሚ እንዲፈናቀሉ ወይም መንግሥት የሰጣቸውን ሕጋዊ ይዞታ ዲዛይን በማጣመምና የሌሎችን ግንባታ ለማዳን ተብሎ የእሳቸውና የመሰሎቻቸው ቤት እንዲፈርስ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ጀምሮ ጡረታ እስከወጡበት ድረስ ለአገራቸው ብዙ ማገልገላቸውን የሚናገሩት አቶ በዛብህ በዚህ ዕድሜያቸው እንደ መጦር “ቤት ይፈርሳል” የሚለውን መስማታቸው እንዳሳዘናቸው አስረድተዋል፡፡ወግ ማዕረግ ያዩበት፣ልጆች ያፈሩበትንና የትዳር አጋራቸውን ያጡበትን ቀያቸውን ለልማት ብለው እንደለቀቁ ሁሉ፣የ100 ዓመታት የዕድሜ ባለፀጋ በድጋሚ ተፈናቀሉ ማለት ተገቢ ባለመሆኑ፣ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊያስተካክል እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
ሌላው የ96 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት አቶ ሙሀባ ነጠረ በልማት ምክንያት የተፈናቀሉት መገናኛ ዳያስፖራ አደባባይ ከሚባለው አካባቢ ሲሆን አሁን በመንገድ ምክንያት በድጋሚ እንደሚፈናቀሉ መነገሩ ተገቢ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከሁለት ጊዜ በላይ የፓርላማ ተመራጭ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ሙሀባ ለአገራቸው መልካም ነገርን መሥራታቸውን በመግለጽ መንግሥት ሊጦራቸው ሲገባ እንዲፈናቀሉ መታሰቡ እንዳሳዘናቸው
ሸራተን አዲስ ከተገነባበት ቦታ ፍል ውኃ አካባቢ የተነሱና በሼክ መሐመድ አል አሙዲ ቤት ተገንብቶላቸው አልታድ ሠፈር ከ20 ዓመታት በላይ የኖሩ እናቶችም በዲዛይን ምክንያት ቤታቸው ሳይቀር እንደሚፈርስ መለካቱን ለሪፖርተር ገልጸዋል:፡