ከጎንደር ከተማ በፖሊስና ደህንነቶች ታፍኖ የተወሰደው የሰማያዊ ፓርቲ አባል መምህር አለላቸው አታለለ የት እንደሚገኝ አልታወቀም ተባለ

ሐምሌ ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሀምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጎንደር ከተማ ውስጥ በፖሊስና ደህንነቶች ታፍኖ የተወሰደው የሰማያዊ ፓርቲ አባል መምህር አለላቸው አታለለ የት እንደሚገኝና በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ እንዳልቻሉና ከፍተኛ ጭንቀት ላይ መሆናቸውን ቤተሰቦቹ አስታውቀዋል
በጎንደር መምህራን ኮሌጅ የአይ ሲቲ መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ የሆነው መምህር አለላቸው አታለለ ፣ ሀምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ደብረታቦር ተወስዶ በደብረታቦር ከተማ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ እንደነበር መረጃ ደርሷቸው ታሰረ የተባለበት ቦታ ድረስ ሄደው ቢጠይቁም እንደሌለ ተነግሯቸዋል፡፡ሌሎች እስር ቤቶች ውስጥ ቢያጠያይቁም ሊያገኙት እንዳልቻሉ ቤተሰቡ አክለው ገልፀዋል።
መምህር አለላቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ከቤተሰቦቹ ጋር ሳይገናኝ የቆየ ሲሆን ከሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ ተወስዷል በመባላቸው አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ እስር ቤቶች ውስጥ እስከ ዛሬ ሀምሌ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ቢጠይቁም እንደሌለ ተነግሯቸዋል ሲል ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
በሌላ በኩል የሰማያዊ ፓርቲ አመራር፥ አቶ አግባው ሰጠኝ ‹‹የታሰርኩት የመተማ መሬት ለሱዳን መሸጡን በመናገሬ ነው” ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።
“ትናንትም መሬቱ መሸጡን ስናገር ቆይቻለሁ፡፡ ወደፊትም እናገራለሁ፡፡ የተከሰስኩት በመሬቱ ጉዳይ ነው እንጅ አሁን የተከሰስኩበትን ወንጀል ፈጽሜ አይደለም፡፡›› ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን ለፍርድ ቤት መስጠቱን ጋዜጣው ዘግቧል።
አመራሮቹ ሀምሌ 1/2007 ዓ.ም በጠበቆቻቸው በኩል የክስ መቃወሚያና የዋስትና ጥያቄ አቅርበው፣ ሀምሌ 13/2007 ዓ.ም አቃቤ ህግ ለጥያቄው መቃወሚያ እንዲያሰማ ቀጠሮ ተሰጥቶት ተቃውሞ ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡ በመሆኑም የተከሳሾቹ ጠበቃዎች ደንበኞቻቸው በሽብር ወንጀል ያልተሳተፉ በመሆናቸው በሽብር ወንጀል መከሰሳቸው ትክክል አለመሆኑን፣ ቢቻል ክሱ ተዘግቶ እንዲሰናበቱ፣ ይህ ባይሆን እንኳ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ያቀረቡትን ጥያቄ መሰረት አድርጎ ብይን እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ለዛሬ ተቀጥሮ ነበር፡፡ ይሁንና ዛሬ ሀምሌ 17/2007 ዓ.ም በልደታ ፍርድ ቤት 14ኛ ምድብ ችሎት በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ‹‹በመረጃ የሚረጋገጥ ይሆናል›› በሚል ጠበቆች ያቀረቡትን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል፡፡
ፍርድ ቤቱ የክስ መቃወሚያውን ውድቅ ካደረገ በኋላ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ በጠየቀው መሰረት 16ቱም አመራሮች የተከሰሱበትን ወንጀል አልፈፀምንም ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሁሉም ተከሳሾቹ የመኢአድ፣ የቀድሞው አንድነትና፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ናቸው፡፡
በዚህ በመቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮነን፣ በላይነህ ሲሳይ፣ አለባቸው ማሞ፣ አወቀ ሞኝሆዴ፣ ዘሪሁን በሬ፣ ወርቅየ ምስጋናው፣ አማረ መስፍን፣ ተስፋየ ታሪኩ፣ ቢሆነኝ አለነ፣ ተፈሪ ፈንታሁን፣ ፈረጀ ሙሉ፣ አትርሳው አስቻለው፣ እንግዳው ቃኘው፣ አንጋው ተገኘ፣ አግባው ሰጠኝና አባይ ዘውዱ ተካተዋል።
በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ የተከሰሱት 16 የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የአቃቤ ህግን ምስክር ለመስማት ለነሃሴ 12ና 13/2007 ዓ.ም ተቀጥረዋል፡፡ በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት በልደታ ፍርድ ቤት የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ተቀጥረው የነበሩት እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ለሀምሌ 28/2007 ዓ.ም ተቀጥረዋል፡፡