ገዢው ፓርቲ የሽብር ተግባር በመፈጸም በግንቦት7 ለማላከክ አቅዷል ሲል አርበኞች ግንቦት7 ከሰሰ

ሐምሌ ፲፸ (አስራሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ግንባሩ ባወጣው መግለጫ “በሕዝባዊ ኃይሎች ላይ ሊወስድ ያሰበው እርምጃ ተቀባይነት እንዲያገኝለት የሽብር ተግባር ፈጽሞ በአርበኞች ግንቦት 7 ላይ ለማላከክ ወስኗል።” ብሎአል።
አርበኞች ግንቦት 7 “በቅርቡ የጀመረው የነፃነት ትግል የፈጠረበት መደናገጥ ለመሸፈንና ንቅናቄውን በኢትዮጵያ ሕዝብና በዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብ ለማስወገዝ ያግዘኛል ብሎ ያመነበት ይህን ዘግናኝ ሴራ ከሳምንት በፊት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁቱን አጠናቆ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ የነፃ ሚዲያ አባላት ደርሰውበት ለሕዝብ ይፋ በማድረጋቸው እንዲዘገይ ” እንዳደረገው ድርጅቱ ጠቅሷል።
አርበኞች ግንቦት7 ደረሰኝ ባለው አስተማማኝ መረጃ መሰረት ” ሴራው ከበፊቱ በባሰ እና ይበልጥ አውዳሚ በሆነ መጠን ተግባራዊ ለማድረግ የህወሓት “ስውር” መንግሥት በመወሰኑ ይህን የማስጠንቀቂያ መግለጫ ለማውጣት መገደዱን ገልጿል።
ህወሓት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ መወሰኑን የሚገልጸው ግንባሩ፣ የእቅዱ ዓላማ ዘግናኝ እርምጃ በንፁሃን ዜጎችና ሕፃናት ላይ በማድረስ “የሽብር ጥቃቶች ሰለባ” ነኝ በማለት የኢትዮጵያ እና የዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ አዘኔታ ለማግኘት በተለይም የዩ. ኤስ. አሜሪካ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን የሚጎበኙ በመሆኑ ይህንን እቅድ ተግባራዊ የማድረግ ጉጉቱ እንዲጨምር እንዳደረገው መግለጫው አመልክቷል።
“የቦሌ ዓለም ዓቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ እና ወደዚያ የሚያደርሰው መንገድ፣ የአፍሪቃ ኅብረት ጽ/ቤት እና የአሜሪካ ኤምባሲ ህወሓት በሽብር ጥቃት ዒላማነት ከመዘገባቸው ውስጥ ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።
አርበኞች ግንቦት 7 በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚቃጡ የሽብር ጥቃቶችን መቃወም ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብሮ እንደሚያመክን፣ በህወሓት የተደገሰውን የሽብር ጥቃት ማምከን እንደሚገባና ይህን እኩይ እቅድ አስቀድሞ አውቆ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አንድ ዓይነተኛ የሽብር መከላከያ ዘዴ መሆኑን ጠቅሷል።
“እያንዳንዱ ዜጋ የህወሓትን እኩይ ሴራ ተገንዝቦ ራሱን፣ ቤተሰቡንና አካባቢውን ከጥቃት እንዲጠብቅ አርበኞች ግንቦት 7 በጥብቅ ያሳስባል። ” ሲል መግለጫውን ደምድሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጎንደር ከተማ ፍተሻው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ የጸጥታ ሃይሎች የአርበኞች ግንቦት7 ታጣቂ ሃይሎች በከተማው ሰርገው ገብተዋል በሚል ህዝቡን እዋከቡት ነው።
ግንባሩ በቅርቡ በአዘዞ የህወሃት ንብረት በሆነው ሱር ኮንስትራክሽን ላይ ጥቃት መፈጸሙን ካስታወቀ በሁዋላ፣ የጸጥታ ሃይሎች በነዋሪዎች ላይ የሚፈጽሙት እንግልት ጨምሯል።
በሌላ በኩል ግንባሩ በጀርመን የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ለነገ ማቀዱን ሃይሉ ማሞ ከስፍራው ዘግቧል።