አቶ በፍቃዱ አበበ የመከላከያ ምስክሮችን አሰማ

ሐምሌ ፲፮ (አስራስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሽብርተኝነት ተከሶ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኘው በአርባ ምንጭ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ ዋና ፀኃፊ አቶ በፍቃዱ አበበ በትናንትናው ዕለት ሀምሌ 15 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት የመከላከያ ምስክሮቹን አሰምቷል፡፡
ከአምስቱ የመከላከያ ምስክሮች መካከል አራቱ ፣ የአርባ ምንጭ ፖሊስና ደህንነቶች በፍቃዱ አበበ ላይ በሀሰት ከመሰከሩ የተሻለ ጥቅም እንደሚሰጣቸው ቃል ገብተውላቸው እንደነበር ገልጸው መስክረዋል፡፡
ከዓመት በፊት አንድነት ፓርቲ በአርባ ምንጭ ከተማ ያደርገው በነበረው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተሳትፈሃል ተብሎ ከድንጋይ ማንጠፍ ማኅበር የተሰናበተ አንድ ወጣት ‹‹በፍቃዱ አበበ ለግንቦት ሰባት እየመለመለ ይልካል፡፡እኔንም መልምሎኛል ብለህ ከመሰከርክ ወደ ስራህ እንመልስሃለን›› እንዳሉትና እሱም ፈቃደኛ ባለመሆኑ በሀሰት ሳይመሰክር መቅረቱን ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ሌላ ወጣት በፍቃዱ ላይ ምስክር ሆኖ ከቀረበ የሚፈልገውን እንዲሚያደርጉለት ቃል ተገብቶለት እንደነበር ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ይህ ወጣት የአቃቤ ህግ ምስክር ሆኖ ልደታ ፍርድ ቤት ድረስ መጥቶ የነበር ቢሆንም በፍቃዱን እንደማያውቀውና በሀሰት መስክር መባሉን እንደሚገልጽ ለአቃቤ ህጉ በመናገሩ ሳይመሰክር እንዲመለስ መደረጉን አስረድቷል፡፡
አቶ በፍቃዱ ተጨማሪ ምስክሮችን ለማሰማት እንዲሁም የአቃቤ ህግ ምስክር ሆኖ በሀሰት መስክሮብኛል ያለው ግለሰብ ለአርባ ምንጭ ፖሊስና ለልደታ ፍርድ ቤት የሰጠው ቃል እንዲቀርብለት በመጠየቁ ተጨማሪ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ለማቅረብ ለነሀሴ 21 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡አቶ በፍቃዱ አበበ በመከላከያ ምስክርነት የጠራቸው ግለሰቦች እንደታሰሩበትና ለምስክርነት የመጡትም ሲጉላሉበት እንደሰነበቱ መግለጹ ይታወቃል፡፡
በተጨማሪም ፕ/ት ባራክ ኦባማ ሲመጣ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሳችሁ መሆኑን ደርሰንበታል በሚል የታሰሩት አቶ መርከቡ ኃይሌና አቶ አበበ ቁምላቸው ለሀምሌ 20 ቀን 207 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ዛሬ ሀምሌ 16 ቀን 2007 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት በዝግ ችሎት የቀረበው አቶ መርከቡ ኃይሌ ለውሳኔ ለሀምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡
በቄራ ፍርድ ቤት የቀረበው አቶ አበበ ቁምላቸው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶበት ለሀምሌ 20 ቀን ተቀጥሯል፡፡አቶ አበበ የጊዜ ቀጠሮ ሲሰጥበት ይህ ለሶስተኛ ጊዜው ሲሆን ደህንነቶች ‹‹ከሌሎች አባላቶች ጋር በመሰባሰብ ሁከት ለመፍጠር እየሰራችሁ ነው›› በሚል ምርመራ እንደሚያደርጉበትና ድብደባም እንደሚፈጽሙበት ገልጾአል፡፡
በተመሳሳይ ሀምሌ 11 ቀን 2007 ዓ.ም ባልታወቀ ምክንያት የታሰረው የቀድሞ አንድነት አባል አቶ ፍቃዱ በቀለ ካሳንቺስ የሚገኘው 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ምድር ቤት ውስጥ ብቻውን ታስሮ እንደሚገኝ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከእስር ዜና ሳንወጣ በዝዋይ ማረሚያ ቤት ለአሥር ወራት በእስር ላይ የቆየው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከዘመዶቹ ውጪ እንዳይጎበኝና የሕክምና ዕርዳታ እንዳያገኝ ተከልክሏል።