ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያውያን አቤቱታ ማሰማታቸውን ቀጥለዋል

ሐምሌ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በበሳውዲ አረቢያ ለረዢም ጊዜ በስደት ቆይተው ወደ ትውልድ ቀያቸው የተመለሱ በአማራ ክልል የሚገኙ ከስደት ተመላሾች ፤በራሳቸው ካፒታል እና ጥረት ለመንቀሳስ ቢሞክሩም “ልዩ ልዩ መሰናክል በመፍጠር የገዢው መንግስት ሊያሰራን አልቻልንም “በማለት ተናግረዋል፡፡‹‹ ከስደት ከተመለስን በኋላ በማህበር ተደራጁ በማለት ቢያደራጁንም የምንሰራበት የእርሻ መሬት ለማግኘት ለአምስት ወራት አሰቃይተውናል፡፡ ›› የሚሉት ከስደት ተመላሾች፣ እንዲሰሩበት የተሰጣቸው መሬት መጠን አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር ድጋፍ እና ክትትል አልተደረገልንም ብለዋል። የገዢው ፓርቲ በተለያዩ ጊዜያት ከስደት ተመላሾችን በማደራጀት በሃገራቸው ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ ድጋፍ አደረግሁ በማለት በሚዲያ ቢናገርም በተግባር የሚታየው እውነታ ግን ፍጹም ተቃራኒ መሆኑን ከስደት ተመላሾች ይናገራሉ፡፡
ከስደት ተመልሰው በእርሻ ስራ ለመሰማራት አነስተኛ መሬት ከተቀበሉ በኋላ መቅረብ ያለበትን ግብአት በወቅቱ ባለማግኘታቸው ከግለሰብ በእጥፍ ዋጋ ገዝተው ለመጠቀም እንደተገደዱ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ በራሳችን ተነሳሽነት እና ጥረት ለመስራት ባደረግነው ልፋት ስኬታማ ወደ መሆን ደረጃ ብንደርስም፤ የገዢው መንግስት አመራሮች ለኛ ባላቸው ጥላቻ በየጊዜው ስራቸውን የሚያደናቅፍ መሰናክል በማድረግ የስራ ተነሳሽነታችንን እየገደሉት ነው ››በማለት ያማርራሉ፡፡
ከስደት ተመላሾች አሁን እየሰሩ ያለው በገዢው መንግስት የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ሳይሆን በአረብ ሃገራት ባካበቱት ልምድ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡
በስደት ላይ የደረሰባቸውን ስቃይ በማሰብ ለዳግመኛ ስደት ላለመዳረግ በሃገራቸው ሰርተው ለመለዎጥ ቢሞክሩም ከመንግስት አመራሮች በኩል የሚታየው አወንታዊ ምላሽ አበረታች አለመሆኑ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል በርካታ ቁጥር ያላቸው ከስደት ተመላሾች ቢኖሩም ፣ በሚሰማሩበት መስክ የሚሰጣቸው ስልጠና ለግብር ይውጣ ያህል እና ለሚዲያ ፍጆታ እንጅ ሰርተን ለመለዎጥ የምንችልበትን መስመር የተከተለ አይደለም በማለት ብሶታቸውን ያሰማሉ።ከሳውድ አረቢያ የተመለሱ አብዛኞቹ ስደተኞች ተመልሰው ወደ ውጭ አገራት መሄዳቸውን ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ የተገኘው መረጃ ያሳያል።