ሐምሌ ፺፻ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በእነ ዘመነ ካሴ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ድረስ ለተጠቀሱት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ቀደም ብሎ እንደተዘገበው በሽብር ወንጀል የተከሰሱት እስረኞች ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር ተገናኝታችሁዋል ከተባልን፣ አቶ አንዳርጋቸው ቀርበው ይጠየቁልን የሚል መከላከያ መልስ ሰጥተው ነበር። ፍርድ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው በአገር ውስጥ መኖራቸው ስለማይታወቅ እባካችሁ ሌላ ምስክር ጥሩ ብሎ ቢለምናቸውም እስረኞች ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ነበር።
አቃቢ ህግ በጽሁፍ በሰጠው መልስ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በእነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ እና በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መዝገብ ላይ ክስ ቀርቦባቸው በእድሜ ልክና በሞት እንዲቀጡ ተወስኖባቸው የህዝባዊ መብታቸው የተሻረ በመሆኑ በምስክርነት ሊቀርቡ አይችሉም የሚል መከራከሪያ ቢያቀርብም፣ ፍርድ ቤቱ ግን አቶ አንዳርጋቸው እንዲቀርቡላቸው የጠየቁት ለዋስ አሊያም ልዩ አዋቂ ምስክር ሆነው ሳይሆን ነበሩበት የተባለውን ጉዳይ ለመናገር ለምስክርነት በመሆኑ፣ ምስክርነትም ግዴታ እንጅ መብት ባለመሆኑ ሰኔ 13/2007 ዓ.ም በእነ ዘመነ ካሴ መዝገብ ለተከሰሱት ተከሳሾች ልደታ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲመሰክሩ ውሳኔ አሳልፏል።
ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው የት እንደሚገኙና ማዘዢያው የት ተብሎ ሊፃፍላቸው እንደሚገባ ጠይቀው ለቃሊቲ ማረሚያ ወይንም ለፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ሊጻፍላቸው እንደሚገባ፣ ካልቀረቡላቸውም ክሳቸው ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር የተገናኘ በመሆኑ አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ አቤቱታ እንደሚያቀርቡ መግለጻቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
ዳኞች የወሰኑት ውሳኔ ተፈጻሚ ይሆናል ብለው እንደማይገምቱ አንድ የህግ ባለሙያ ለኢሳት ገልጸዋል። አቶ አንዳርጋቸው ፍርድ ቤት ቀርበው ይመሰክራሉ ብለው እንደማይጠብቁ፣ ይልቁንም ጉዳዩን የያዙት ዳኞች ሊቀየሩ እንደሚችሉ እኝሁ የህግ ባለሙያ ተናግረዋል። የዳኞችን ውሳኔ ያደነቁት ባለሙያው፣ አስፈጻሚው አካል ውሳኔውን እንደሚቀለብሰው ጥርጥር የለኝም ሲሉ አክለዋል።