ሙስሊሙ ማህብረሰብ ለመሪዎቹ ያለውን ድጋፍ ገለጸ

ሐምሌ ፫ (ሶስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሰሞኑን በእስር ላይ የሚገኙ የድምጻችን ይሰማ የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላትን ጥፋተኛ ማለቱን ተከትሎ ፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዛሬ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ድምጹን አሰምቷል።
በቤኒን መስጊድ እጅግ በርካታ ህዝብ በተገኘበት በተደረገው ተቃውሞ ሙስሊሙ ህዝብ፣ የመሪዎቹን ነጻነት ከሚያረጋግጠው የፍርድ ቤት ውሳኔ ውጭ ሌላ ውሳኔ እንደማይቀበል ግልጽ አድርጓል።
ፍርድ ቤት በዚህ ወር መጨረሻ የሚሰጠውን ውሳኔ ተከትሎ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የማያቋርጥ ተቃውሞ እንደሚያደርግ አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ሙስሊም ኢትዮጵያዊ ከአዲስ አበባ ለዘጋቢያችን ተናግሯል። ኮሚቴው እስከሚፈታና ጥያቄያችን እስከሚመለስ ትግሉ አይቆምም የሚለው ወጣቱ፣ ፍርድ ቤት የቱንም ያክል ውሳኔ ቢያሳልፍ ማንም ሙስሊም እንደማይቀበለው ተናግሯል።