ሐምሌ ፫ (ሶስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዛሬ ሐምሌ 3/2007 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋ ሮቢት ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ቤታቸውን ድረስ በመሄድ ፖሊስ እያደነ እንዳሰራቸው የአይን እማኞች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ከጠዋቱ 4 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ፖሊስ የሰማያዊ ፓርቲ የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ የነበሩትን አቶ ዘነበ ደሳለኝ፣ የፓርቲው ንብረት ያዥ የሆኑትን አቶ መንግስቱ ተበጀና የቀድሞው አንድነት የቀጠና አመራርና በአሁኑ ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ቴዎድሮስ ሀብቴ ከእየቤታቸው ተይዘው ታስረዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በተያዙበት ወቅት በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባና እንግልት እንደደረሰባቸውና ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን ምንጮቹ አክለው ገልፀው ከተያዙት አመራሮች በተጨማሪም ሌሎች የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላትም በፖሊስ እየታደኑ መሆናቸውም ተነግርዋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የታገደው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ( መኢአድ ) ፕሬዝደንት አቶ ማሙሸት አማረ የተከሰሰበት ክስ ለሀገር ደህንነት የሚያሰጋ ነው በሚል ሰበብ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተወስኖበታል።
አቶ ማሙሸት አማረ ሰኔ 10/2007 ዓም አራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርቦ በ5 ሺ ብር ዋስ እንዲፈታ ተወስኖለት ነበር። ፓሊስ አለቅም በማለት ይግባኝ ጠይቆ ለ 14 ቀናት በእስር ቤት ካሰቃየው በሁዋላ፣ ቅሊንጦ አቆይቶ አራዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦታል። አቃቢ ህግ “የተከሰሰበት ወንጀል ከባድና ለሀገር ደህንነት አስጊ ነው ምስክሮችንም ሊያስጠፋብን ይችላል ” በማለቱ ፍርድ ቤት ይህንን አጽድቆ፣ ጉዳዩ በአራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ይታይ በሚል መዝገቡን ዘግቶ ፣ አቶ ማሙሸትም እንዲታሰሩ ፈርዶ አሰነብቷል።