ሐምሌ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ጸሀፊና መምህርት ርእዮት አለሙ በሽብር ወንጀል ተከሳ የ14 አመታት ጽኑ እስራት ከተፈረዳበት በሁዋላ፣ ለጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቷ የእስር ጊዜዋ ወደ 5 አመት ዝቅ እንዲል ተደርጎላታል። ያለፉትን ሶስት አመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ በእስር ቤት ካሳለፈች በሁዋላ ፣ የኢህአዴግ መንግስት አመክሮ ጊዜዋ አልቋል በሚል ፈቷታል።
ርዕዮት በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የጽናት ምልክት ተደርጋ ትወሰዳለች። ይህ ጽናቷ አሁንም አብሯት እንዳለ እህቷ እስከዳር አለሙ ለኢሳት ተናግራለች። የርእዮትን መፈታት ያልጠበቁት መሆኑን የገለጸቸው እስከዳር ፣ ቤተሰቦቿ በሙሉ በደስታ ውስጥ መሆኑዋን ገልጻለች
ርእዮት ከመፈታቱዋ ቀደም ብሎ ዞን 9 በመባል የሚታወቁት ወጣት ጸሃፊዎችና ጋዜጠኞች ኤዶም ካሳየ፣ ዘላለም ክበረት፣ ተስፋለም ወልደየስ፣ ማህሌት ፋንታሁንና ዘላለም ክብረት ከእስር ተለቀዋል።
መንግስት ለመፈታታቸው የሰጠው ምክንያት ባይኖርም ብዙ አስተያየት ሰጪዎች የኢህአዴግ መንግስት ፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉብኝት ተከትሎ ፣ ለመፍታት እንደተገደደ ይገልጻሉ።
ሌሎች ወገኖች በበኩላቸው ኢህአዴግ ከኤርትራ ጋር ለሚያደርገው ሙሉ ጦርነት የህዝቡን ድጋፍ ለማግኘት አስቀድሞ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ስለጀመረ ነው ይላሉ።
ሲጄፔ የጻፊዎችን መፈታት በመልካም ጎኑ ተቀብሎ፣ ሌሎች በእስር ቤት ያሉት የዞን 9 አባላትና ጋዜጠኞችም እንዲፈቱ ጠይቋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባን አዲስ ማስተር ፕላን በመቃወም በኦሮምያ ተደርጎ የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ ታስረው ከሚገኙት ቁጥራቸው በውል ከማይታወቅ መካካል 6ቱ መፈታታቸው ታውቋል። ዱኛ ኬሶ፣ ቢሉሱማ ዳመና፣ ሌንጂሳ አለማያሁ፣ አብዲ ከማል፣ መገርሳ ወርቁና ቶፊክ ረሺድ ለወንጀል የሚያበቃ ክስ ሳይመሰረትባቸው ቆይቷል።